ኤርምያስ 20
20
ኤርምያስና ጳስኮር
1በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አለቃ የነበረው፣ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር እነዚህን ነገሮች ኤርምያስ እንደ ተነበየ በሰማ ጊዜ፣ 2ነቢዩ ኤርምያስን መታው፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በላይኛው የብንያም በር በእግር ግንድ ጠረቀው። 3በማግስቱም ጳስኮር ኤርምያስን ከተጠረቀበት ግንድ አወጣው፤ ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ከእንግዲህ ማጎርሚሳቢብ#20፥3 ማጎርሚሳቢብ ማለት ዙሪያ-ገባው ሽብር ማለት ነው። ብሎ ይጠራሃል እንጂ ጳስኮር አይልህም፤ 4እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘አንተንና ወዳጆችህ ሁሉ ለሽብር እዳርጋለሁ፤ የገዛ ዐይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። ይሁዳን ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል። 5የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን፣ የይሁዳን ነገሥታት ውድ ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ። 6ጳስኮር ሆይ፤ አንተና በቤትህ የሚኖሩት ሁሉ ወደ ባቢሎን ትጋዛላችሁ። አንተና በሐሰት ትንቢት የተነበይህላቸው ወዳጆችህ በዚያ ትሞታላችሁ፤ በዚያም ትቀበራላችሁ።’ ”
የኤርምያስ ማጕረምረም
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ አታለልኸኝ፤#20፥7 ወይም ሐሳቤን አስለወጥኸኝ እኔም ተታለልሁ፤
አንተ ከእኔ እጅግ በረታህ፤ አሸነፍህም፤
ቀኑን ሙሉ ማላገጫ ሆንሁ፤
ሁሉም ተዘባበቱብኝ።
8በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤
“ሁከትና ጥፋት!” ብዬ ዐውጃለሁ፤
ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣
ቀኑን ሙሉ ስድብና ነቀፋ አስከተለብኝ።
9ነገር ግን፣ “ከእንግዲህ የርሱን ስም አላነሣም፤
በስሙም አልናገርም” ብል፣
ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣
በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤
ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ፤
ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም።
10“በየቦታው ሽብር አለ፤
አውግዙት፤ እናውግዘው፤”
ብለው ብዙ ሲያንሾካሽኩ ሰማሁ፤
መውደቄን በመጠባበቅ፣
ባልንጀሮቼ የነበሩ ሁሉ፣
“ይታለል ይሆናል፣
ከዚያም እናሸንፈዋለን፤
እንበቀለዋለንም” ይላሉ።
11ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ኀያል ተዋጊ ከእኔ ጋራ ነው፤
ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ እንጂ አያሸንፉም፤
ክፉኛ ይዋረዳሉ እንጂ አይሳካላቸውም፤
ውርደታቸውም ከቶ አይረሳም።
12ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤
ጕዳዬን ለአንተ አሳልፌ ሰጥቻለሁና
ስትበቀላቸው ለማየት አብቃኝ።
13ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ለእግዚአብሔር ምስጋናን አቅርቡ፤
የድኻውን ነፍስ፣
ከክፉዎች እጅ ታድጓልና።
14የተወለድሁባት ዕለት የተረገመች ትሁን፤
እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን አትባረክ።
15“ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል” ብሎ፣
ለአባቴ የምሥራች የነገረ፣
ደስ ያሠኘውም ሰው የተረገመ ይሁን።
16ያ ሰው እግዚአብሔር ሳይራራ፣
እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፤
በማለዳ ዋይታን፣
በቀትርም የጦርነትን ውካታ ይስማ፤
17እናቴ መቃብር ትሆነኝ ዘንድ፣
ማሕፀንም ሰፊ የዘላለም ማደሪያዬ እንዲሆን፣
ከማሕፀንም ሳልወጣ አልገደለኝምና።
18ችግርና ሐዘንን ለማየት፣
ዘመኔንም በውርደት ለመፈጸም፣
ለምን ከማሕፀን ወጣሁ?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.