የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 የጴጥሮስ መልእክት 3

3
የጌታ ኢየሱስ የመምጣት ተስፋ
1ወዳጆች ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፤ ሁለቱንም መልእክቶች የጻፍኩላችሁ እነዚህን ነገሮች በማስታወስ ቅን አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ላነቃቃችሁ ብዬ ነው። 2ከዚህ በፊት ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና በእናንተ ሐዋርያት አማካይነት ያገኛችሁትን የጌታችንንና የአዳኛችንን ትእዛዝ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ። 3ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያፌዙና ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ፤ #ይሁዳ 18። 4እነርሱ “ጌታ ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተሰጥቶ አልነበረምን? ታዲያ፥ የት አለ? የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ ሁሉ ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እንደ ነበረው ነው” ይላሉ። 5እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማይ በእግዚአብሔር ቃል መፈጠሩን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው ይክዳሉ። #ዘፍ. 1፥6-9። 6በዚያን ጊዜ የነበረውም ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። #ዘፍ. 7፥11። 7እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች አሁን ያሉት ሰማይና ምድር እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቈያሉ።
8ወዳጆቼ ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። #መዝ. 90፥4። 9አንዳንድ ሰዎች እንደሚመስላቸው ጌታ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም ሰው እንዳይጠፋ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሣል።
10የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል፤ #ማቴ. 24፥43፤ ሉቃ. 12፥39፤ 1ተሰ. 5፥2፤ ራዕ. 16፥15። 11እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ ታዲያ፥ እናንተ በቅድስናና እግዚአብሔርን በማምለክ መኖር እንዴት አይገባችሁም? 12እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና በቶሎም እንዲመጣ የምትሠሩ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማይ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል፤ ፍጥረቶችም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤ 13ነገር ግን እኛ በሰጠን ተስፋ መሠረት የጽድቅ ሥራ የሚመሠረትበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን። #ኢሳ. 65፥17፤ 66፥22፤ ራዕ. 21፥1።
14ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህ ሁሉ የሚሆንበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ካላችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤ 15የጌታችንም መታገሥ ለእናንተ መዳን መሆኑን ዕወቁ፤ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስም በተሰጠው ጥበብ መጠን የጻፈላችሁ ይህንኑ ነው። 16እርሱ ስለዚህ ጉዳይ በመልእክቶቹ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ጽፎአል፤ በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ወላዋዮች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህንም ነገሮች ያጣምማሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ለጥፋታቸው ነው።
17እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ ከጽኑ አቋማችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤ 18ይልቅስ በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እርሱንም በማወቅ ከፍ ከፍ በሉ፤ ለእርሱ አሁንም ለዘለዓለምም ክብር ይሁን! አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ