የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 23

23
ሰውን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ የሚለይ ሁኔታ
1“የተኰላሸ ወይም የተሰለበ ሰው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባል አይሁን።
2“ከጋብቻ ውጪ ዲቃላ ሆኖ የተወለደና የእርሱም ዘር ሆኖ የተወለደ ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ገብቶ አይቈጠር።
3“ዐሞናዊም ሆነ ሞአባዊ ወይም የእነርሱ ዘር የሆነ ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባል አይሁን። 4እናንተ ከግብጽ ምድር ወጥታችሁ በጒዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እነርሱ እህልና ውሃ አንሰጥም ብለው ከልክለዋችሁ እንደ ነበር አይዘነጋም፤ ከዚሁም ጋር በመስጴጦምያ ፐቶር ተብላ በምትጠራው ከተማ ይኖር የነበረ የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲረግማችሁ ቀጥረውት ነበር። #ዘኍ. 22፥1-6። 5ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክህ እርሱን ማዳመጥ አልፈለገም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር አንተን ስለሚወድህ መርገሙን ወደ በረከት ለወጠው። እግዚአብሔር እናንተን ይወዳችኋል። #ነህ. 13፥1-2። #ዘኍ. 23፥7—24፥9። 6በምትኖርበት ዘመን ሁሉ እነዚህ ሕዝቦች ባለጸጎች ሆነው በሰላም እንዲኖሩ አትርዳቸው።
7“ኤዶማውያን ዘመዶችህ ስለ ሆኑ አትጸየፋቸው፤ በግብጽ ምድር ስደተኛ ሆነህ ስለ ኖርክ ግብጻውያንን አትጸየፋቸው። 8የእነርሱም ከሦስተኛው ትውልድ በኋላ ዘሮቻቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ አባሎች ይሁኑ።
የጦር ሰፈርን በሕጉ መሠረት በንጽሕና ስለ መጠበቅ
9“በጦርነት ጊዜ በጦር ሰፈር ውስጥ ስትገኙ፥ ርኩስ ነገርን ሁሉ አስወግዱ። 10አንድ ሰው ሌሊት በሕልሙ ከአባለ ዘሩ የፈሰሰ እርጥበት በሰውነቱ ላይ ቢገኝ ከሰፈር ወጥቶ በዚያው ይቈይ። 11ወደ ማታም ጊዜ ገላውን ይታጠብ፤ ጀንበር ስትጠልቅም ወደ ሰፈር ይመለስ።
12“የምትጸዳዱበትን ልዩ ስፍራ ከሰፈር ውጪ አዘጋጁ፤ 13በምትጸዳዱበት ጊዜ እዳሪ ለመቈፈርና መልሶ ለመድፈን የሚያገለግላችሁን አንካሴ ከጦር መሣሪያችሁ ጋር ያዙ። 14ሰፈራችሁን በሕጉ መሠረት በንጽሕና ጠብቁ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ሊጠብቃችሁና በጠላቶቻችሁም ላይ ድልን ሊያጐናጽፋችሁ በሰፈራችሁ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ፊቱን ከእናንተ እንዲመልስ የሚያደርገውን አስነዋሪ ነገር ሁሉ አታድርጉ።
ልዩ ልዩ ሕግጋት
15“አንድ ባሪያ ከጌታው በመኰብለል ወደ አንተ መጥቶ ቢጠጋ፥ ለጌታው አሳልፈህ አትስጠው። 16ከከተሞችህ በአንዱ በመረጠው ስፍራ ከአንተ ጋር በመካከልህ ይኑር እንጂ አታስጨንቀው።
17“እስራኤላዊ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት የቤተ ጣዖት ተከታዮች እንደሚያደርጉት የዝሙት ሥራ አይፈጽሙ፤ #ዘሌ. 19፥29። 18እግዚአብሔር ዝሙትን ስለሚጠላ በዚህ ተግባር የተገኘ ገንዘብ የስእለትን መፈጸም የሚያመለክት ስጦታ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር አምላክህ ቤት አይግባ።
19“ለእስራኤላዊ ወገንህ ገንዘብ ብታበድረው ወይም ምግብ የሚሆንና ሌላም ነገር ብትሰጠው፥ ወለድ አትጠይቀው። 20ወለድ መጠየቅ የሚገባህ ከውጪ አገር ተወላጅ እንጂ ከእስራኤላዊ ወገንህ አይደለም፤ ይህን ሕግ ፈጽም፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሄደህ በምትወርሳት ምድር የምትሠራውን ሁሉ ይባርክልሃል። #ዘፀ. 22፥25፤ ዘሌ. 25፥36-37፤ ዘዳ. 15፥7-11።
21“ለእግዚአብሔር አምላክህ ስእለት በምታደርግበት ጊዜ ለመስጠት ወይም ለመፈጸም ቃል የገባህበትን ስእለት አታዘግይ፤ እግዚአብሔር አንተ የገባኸውን ቃል እንድትፈጽም ይፈልጋል፤ ስእለትህን ካልፈጸምክ ግን ኃጢአት ይሆንብሃል። #ዘኍ. 30፥1-16፤ ማቴ. 5፥33። 22ይሁን እንጂ ለእግዚአብሔር ስእለት አለማድረግ ራሱ ኃጢአት አይደለም፤ 23ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍላጎትህ በተሳልከው መሠረት፥ አፍህ የተናገረውን በጥንቃቄ መፈጸም አለብህ።
24“በአንድ ሰው የወይን ተክል መካከል በምታልፍበት ጊዜ ከፍሬው የምትፈልገውን ያኽል ብላ፤ ነገር ግን በማናቸውም ዕቃ ከፍሬው አትውሰድ። 25በአንድ ሰው የእህል ማሳ ውስጥ በምታልፍበትም ጊዜ እሸቱን በእጅህ እየቈረጥህ መብላት ትችላለህ፤ ነገር ግን ሰብሉን አጭደህ አትውሰድ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ