ኦሪት ዘዳግም 33
33
ሙሴ የእስራኤልን ነገድ ሁሉ እንደ ባረከ
1የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት የእስራኤልን ሕዝብ የባረከበት ቃለ በረከት ይህ ነው፦
2ሙሴም እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር ከሲና ተራራ መጣ፤
ከኤዶም ላይ እንደ ንጋት ፀሐይ አበራ፤
ከፋራንም ተራራ ላይ አንጸባረቀ፤
በስተቀኙ የእሳት ነበልባል ነበር፤
ከእርሱም ጋር አእላፍ መላእክት ነበሩ።
3እግዚአብሔር በእውነት ሕዝቡን ይወዳል፤
ቅዱሳኑን ሁሉ ይጠብቃል፤
እነርሱም በእግሩ ሥር ተንበርክከው ይሰግዳሉ፤
መመሪያውንም ይቀበላሉ፤
4የእስራኤል ሕዝብ ርስት የሆነውን፥
ሙሴ የሰጠንን ሕግ ይጠብቃሉ።
5የእስራኤል ነገዶችና የሕዝቡ መሪዎች በተሰበሰቡ ጊዜ፥
እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ነገሠ።”
6ሙሴ ሰለ ሮቤል ነገድ እንዲህ አለ፦
“ምንም እንኳ ብዛቱ ጥቂት ቢሆን፥
ጌታ ሆይ የሮቤል ነገድ ይኑር እንጂ አይሙት።”
7ስለ ይሁዳ ነገድም እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር ሆይ፥ የይሁዳን ነገድ ጩኸት ስማ፤
ከሌሎች ነገዶች ጋር እንዲተባበር አድርግ፤
የበረታ ኀይል ስጣቸው፤
ከጠላቶቻቸው ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ርዳቸው።”
8ስለ ሌዊም ነገድ እንዲህ አለ፦
“ጌታ ሆይ! በቱሚምና በዑሪም አማካይነት
በማሳና በመሪባ ውሃ ዘንድ ተከራክረህ ለፈተንካቸው
ለአገልጋዮችህ ለሌዋውያን ፈቃድህን ግለጥ። #ዘፀ. 17፥7፤ ዘኍ. 20፥13።
9እነርሱ ለአንተ ሲሉ ወላጆቻቸውን ረስተዋል፤
ከዘመዶቻቸው ተለይተዋል፤
ልጆቻቸውን ትተዋል፤
ቃልህን አክብረዋል።
ቃል ኪዳንህንም ጠብቀዋል፤
10ሥርዓትህን ለያዕቆብ፥
ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤
በፊትህ ዕጣን ያጥናሉ፤
የሚቃጠል መሥዋዕትም
በመሠዊያህ ላይ ያቀርባሉ።
11አምላክ ሆይ! ሀብታቸውን ባርክ፤
የእጃቸውን ሥራ ተቀበል፤
የጠላቶቻቸውን ኀይል አድክም፤
የሚጠሉአቸውም ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ አድርግ!”
12ስለ ብንያምም ነገድ እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር የሚወደው ያለ ስጋት ይረፍ፤
ኀያሉ አምላክ ቀኑን ይጠብቀዋል።
በእግዚአብሔር ጥበቃም ሥር ይኖራል።”
13ስለ ዮሴፍም ነገድ እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር ከላይ በሰማይ በሚዘንብ ዝናብ፥
ከታችም ከጥልቀት በሚገኘው ውሃ፥
ምድራቸውን ይባርክ።
14እንዲሁም በፀሐይ በበሰለ ምርጥ ፍሬ የተመላ ይሁን፤
በየወቅቱም ብዙ ምርት ይስጥ።
15እንዲሁም ከጥንት የነበሩ ተራሮቻቸውና
ከኮረብቶቻቸው በተትረፈረፈ ምርጥ ምርት የበለጸጉ ይሁኑ፤
16ምድራቸው ምርጥ በሆነ ነገር ሁሉ የተመላ ይሁን፤
በሚቃጠለው ቊጥቋጦ ውስጥ ከተገለጠው አምላክ ጸጋ ይብዛለት።
ከወንድሞቹ መካከል ግንባር ቀደም ለሆነው ልዑል ለዮሴፍ ይደረግለት።
17የዮሴፍ ግርማ እንደ ኰርማ አስፈሪ ነው፤
ቀንዶቹም እንደ ጐሽ ቀንዶች ጠንካሮች ናቸው፤
በእነርሱም ሕዝቦችን ይወጋል፤
እስከ ምድር ዳርቻም ያባርራል፤
የኤፍሬም ዐሥር ሺሆች
የምናሴም ሺሆች እንደዚያው ናቸው።”
18ስለ ዛብሎን ስለ ይሳኮር ነገዶችም እንዲህ አለ፦
“ዛብሎን በመርከብ ስትጓዝ ደስ ይበልህ፤
ይሳኮርም በቤትህ ሆነህ ደስ ይበልህ።
19ሕዝቦችን ወደ ተራራ ጠርተው
እዚያ ትክክለኛ የሆነውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤
ከባሕር ሀብትን፥
ከአሸዋም ድብቅ የሀብት ክምችትን ያገኛሉ።”
20ስለ ጋድ ነገድም እንዲህ አለ፦
“የጋድን ግዛት ያሰፋ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤
ጋድ ክንድን ወይም ግንባርን ለመስበር፥
እንደ አንበሳ ያደባል።
21የመሪነት ድርሻ ስለ ተቀመጠለት፥
ለራሱ የተሻለውን መሬት መረጠ፤
የሕዝብ አለቆች በተሰበሰቡ ጊዜ
የእግዚአብሔርን ፈቃድና
ሥርዓቱን ለእስራኤል ፈጸመ።”
22ስለ ዳንም ነገድ እንዲህ አለ፦
“ዳን እንደ አንበሳ ደቦል ነው፤
እርሱ ከባሳን ይዘላል።”
23ስለ ንፍታሌም ነገድ እንዲህ አለ፦
“ንፍታሌም በጌታ ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው፤
በእግዚአብሔር በረከትም ተሞልቶአል፤
ግዛቱም እስከ ባሕሩና ወደ ደቡብ የተዘረጋ ነው።”
24ስለ አሴር ነገድም እንዲህ አለ፦
“አሴር ከሌሎች ነገዶች ሁሉ ይበልጥ የተባረከ ይሁን፤
እርሱም በወንድሞቹ ዘንድ የተወደደ ይሁን፤
ምድሩም በወይራ ዛፍ የበለጸገች ትሁን።
25የከተሞችህ በሮች በብረትና በናስ የተጠናከሩ ይሁኑ።
በዘመንህ ሁሉ ኀይል ይኑርህ።”
26የእስራኤል ሕዝብ ሆይ!
በሰማያዊ ግርማው አንተን ለመርዳት በሰማይና በደመና ላይ
እንደ እኛ አምላክ እንደ እግዚአብሔር
ማንም የለም
27ዘለዓለማዊ አምላክ መጠጊያህ
ዘለዓለማዊ ክንዶቹ ደጋፊዎች ናቸው፤
ጠላትን ከፊትህ ያባርራል፤ እንድትደመስሳቸውም ያደርጋል።
28ስለዚህ የያዕቆብ ዘሮች
ከሰማይ ጠል በሚወርድባት፥
እህልና የወይን ጠጅ በሞላባት ምድር
ዋስትና አግኝተው በሰላም ይኖራሉ።
29እስራኤል ሆይ! የእርዳታህ ጋሻ፥
የድልህ ሰይፍ
መዳንን ከእግዚአብሔር ያገኘ፥
እንዳንተ ያለ ሕዝብ ከቶ የለም፤
ምንኛ የታደልክ ነህ!
ጠላቶች እየተለማመጡ ወደ አንተ ሲመጡ
ጀርባቸውን ትረግጣለህ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 33: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997