የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 13

13
በኲር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለ መሆኑ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ከእስራኤል ሕዝብም ሆነ ከእንስሶቹ በኲር ሆኖ የተወለደ ሁሉ ለእኔ መሆን ይገባዋል፤ ስለዚህ በኲር ሆኖ የተወለደውን ሁሉ ለእኔ እንዲሆን ቀድሰው።” #ዘኍ. 3፥13፤ ሉቃ. 2፥23።
የቂጣ በዓል
3ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ይህ ቀን በባርነት ስትገዙ የኖራችሁበትን የግብጽን ምድር ለቃችሁ የወጣችሁበት ስለ ሆነ ይህን ቀን አስታውሱ፤ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ በመታደግ ያወጣችሁ በዚህ ቀን ነው፤ ስለዚህ በዚህ ቀን እርሾ የነካው እንጀራ አትብሉ። 4በዚህ ቀን፥ የዓመቱ መጀመሪያ በሆነው በአቢብ ወር ግብጽን ለቃችሁ ወጥታችኋል። 5የከነዓናውያንን፥ የሒታውያንን፥ የአሞራውያንን፥ የሒዋውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር እንደሚያወርሳችሁ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ በመሐላ ቃል ኪዳን ገብቶአል፤ በማርና በወተት ወደ በለጸገችው ወደዚያች ለም ምድር በሚያገባችሁ ጊዜ በዓመቱ መጀመሪያ ወር ላይ ይህን በዓል ታከብሩታላችሁ። 6ሰባት ቀን ሙሉ እርሾ የሌለበት ቂጣ ትበላላችሁ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር ክብር በዓል ታደርጋላችሁ። 7እስከ ሰባት ቀን ድረስ ያልቦካ እንጀራ ትበላላችሁ፤ እርሾም ሆነ የቦካ እንጀራ ከቶ በምድራችሁ አይገኝ። 8በዓሉም በሚከበርበት ጊዜ ይህን ሁሉ የምታደርጉት ከግብጽ በወጣችሁበት ጊዜ እግዚአብሔር ያደረገላችሁን መልካም ነገር ሁሉ ለማስታወስ መሆኑን ለልጆቻችሁ ተርኩላቸው። 9ይህም በዓል በእጃችሁ እንደ ታሰረ ምልክትና በግንባራችሁ እንዳለ ማስታወሻ ይሆንላችኋል፤ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ ከግብጽ ስላወጣችሁም የእግዚአብሔር ሕግ ዘወትር ከአንደበታችሁ ሳይለይ በቃላችሁ እንድትደግሙትና እንድታጠኑት ያስታውሳችኋል። 10ስለዚህ ይህን በዓል በየዓመቱ በተመደበለት ጊዜ የማክበር ሥርዓት ይሁንላችሁ።
የበኲር ልጅ
11“እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀድሞ አባቶቻችሁ ለመስጠት ቃል ወደገባላችሁ ወደ ከነዓናውያን ምድር ያመጣችኋል፤ ይህችንም ምድር በሚያወርሳችሁ ጊዜ፥ 12በኲር የሆነውን ወንድ ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ፤ እንዲሁም የእንስሶቻችሁ በኲር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። #ዘፀ. 34፥19-20፤ ሉቃ. 2፥23። 13ከአህያ የተወለደውን በኲር ግን የበግ ጠቦት በመተካት ከእግዚአብሔር እጅ ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ለመዋጀት ካልፈለጋችሁ ግን አንገቱን ስበሩት፤ በኲር የሆነውንም ወንድ ልጅ ሁሉ መዋጀት ይገባችኋል። 14በሚመጡት ዘመናት ልጆችህ የዚህን ሥርዓት ትርጒም ቢጠይቁህ፥ እንዲህ በማለት ታስረዳቸዋለህ፦ ‘በባርነት ከተገዛንበት ከግብጽ ምድር እግዚአብሔር በታላቅ ኀይል አወጣን፤ 15የግብጽ ንጉሥ ልቡን አደንድኖ እልኸኛ በመሆን አለቃችሁም ባለ ጊዜ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር የሰውንም ሆነ የእንስሶችን በኲር ሁሉ ገደለ፤ በኲር ሆኖ የተወለደውን ወንድ እንስሳ መሥዋዕት አድርጌ የማቀርበው በዚህ ምክንያት ነው፤ በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ልጆቻችንን ግን እንዋጃቸዋለን። 16ይህም ሥርዓት በእጃችን እንደ ታሰረና በግንባራችን ላይ እንደሚገኝ ምልክት ማስታወሻ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ ከግብጽ ምድር እንዳወጣንም ያስታውሰናል።’ ”
የደመና ዐምድና የእሳት ዐምድ
17የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ቅርብ በሆነው በፍልስጥኤም የባሕር ጠረፍ በኩል ባለው መንገድ አልመራቸውም፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ሕዝቡ ከፊት ለፊታቸው ጦርነት እንደሚጠብቃቸው በሚያዩበት ጊዜ ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብጽ እንዳይመለሱ ነው። 18ስለዚህ ይህን በማድረግ ፈንታ ወደ ቀይ ባሕር በሚያመራው በረሓ፥ ዘወርዋራ በሆነ መንገድ መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ።
19ዮሴፍ “እግዚአብሔር ታድጎአችሁ በምትወጡበት ጊዜ ዐፅሜን ከዚህች ምድር ይዛችሁ እንድትወጡ” በማለት ተናግሮ ስለ ነበረ አስከሬኑን እንዲወስዱ እስራኤላውያንን በመሐላ ቃል ኪዳን ባስገባቸው መሠረት ሙሴ የዮሴፍን አስከሬን ይዞ ሄደ። #ዘፍ. 50፥25፤ ኢያሱ 24፥32።
20እስራኤላውያን ከሱኮት ተነሥተው በበረሓው ዳርቻ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ፤ 21ቀንና ሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር ቀን በደመና ዐምድ፥ ሌሊት ደግሞ ብርሃን በሚሰጥ በእሳት ዐምድ ይመራቸው ነበር፤ 22በዚህ ዐይነት የደመናው ዐምድ በቀን፥ የእሳቱ ዐምድ በሌሊት ዘወትር እፊት እፊታቸው ይገኝ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ