ኦሪት ዘጸአት 26
26
የተቀደሰው ድንኳን
(ዘፀ. 36፥8-38)
1“እንዲሁም የተቀደሰውን ድንኳን ውስጠኛ ክፍል ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ በፍታ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች አብጀው፤ በእነርሱም ላይ ኪሩቤል በጥልፍ ጥበብ እንዲሳሉ አድርግ። 2እያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ሜትር የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ሆኖ ሁሉም እኩል ይሁኑ። 3አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ይሁኑ፤ ሌሎቹም አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው በመገጣጠም ተሰፍተው በሌላ በኩል ይሁኑ። 4ተገጣጥመው በተሠሩት በሁለቱም መጋረጃዎች በየአንዳንዱ ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶችን አድርግ። 5በመጀመሪያው መጋረጃ መጀመሪያ ክፍል ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሁለተኛው መጋረጃ መጨረሻ ክፍል ላይ ከሌሎቹ ቀለበቶች ፊት ለፊት ኀምሳ ቀለበቶች አድርግ። 6የተቀደሰው ድንኳን አንድ ይሆን ዘንድ ለእነዚህ ሁለት ክፍሎች ኀምሳ የወርቅ መያዣዎችን ሠርተህ በቀለበቶቹ አገጣጥማቸው።።
7“ከፍየል ጠጒር የተሠሩ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ለድንኳኑ ክዳን አድርግ። 8የእያንዳንዱ ርዝመት ዐሥራ ሦስት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሁለት ሜትር ሆኖ የሁሉም መጠን እኩል ይሁን። 9አምስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱን በሌላ በኩል አድርገህ በአንድነት በማጋጠም ስፋቸው፤ ስድስተኛው መጋረጃ ታጥፎ ከፊት በኩል በድንኳኑ ላይ ይደረብ። 10በአንድ በኩል ካለው መጋረጃ መጨረሻ ክፍል ጠርዝ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሌላም በኩል ካለው መጋረጃ መጨረሻ ጠርዝ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11በቀለበቶቹም ውስጥ ኀምሳ የነሐስ መያዣዎችን አስገባ፤ በዚህም ዐይነት ሁለቱን ክፍሎች በማገጣጠም አንድ ክዳን እንዲሆኑ አድርግ። 12ትርፍ የሆነውን ግማሽ መጋረጃ ወስደህ በድንኳኑ ጀርባ አንጠልጥለው። 13በርዝመቱ በኩል ከእያንዳንዱ መጋረጃ ትርፍ ሆነው የቀሩት ግማሽ ሜትር ስፋት ያላቸው መጋረጃዎች በጐንና ጐን ተንጠልጥለው ድንኳኑን ይሸፍኑት።
14“ለውጪው ክዳን ይሆኑ ዘንድ፥ አንደኛው ቀይ ቀለም ከተነከረ አውራ በግ ቆዳ፥ ሌላው ከተለፋ የፍየል ቆዳ ሁለት ተጨማሪ ክዳኖችን ሥራ።
15“ድንኳኑን የሚደግፉ ቋሚ ተራዳዎች ከግራር እንጨት ሥራ። 16እያንዳንዱ ተራዳ ርዝመቱ አራት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ይሁን። 17የተራዳ ሁለት ሳንቃዎች መገጣጠም ይችሉ ዘንድ ለእያንዳንዱ ተራዳ ማያያዣዎች ይኑሩት። ለማደሪያው ተራዳዎችም ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18ከድንኳኑ በስተ ደቡብ በኩል ኻያ ተራዳዎችን አድርግ፤ 19በእነርሱም ሥር አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ሁለቱን ተራዳዎች ለማያያዝ እንዲረዱ እያንዳንዱ ተራዳ ሁለት እግሮች ይኑሩት። 20ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ኻያ ተራዳዎችን አድርግ፤ 21በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት እግሮችን በመሥራት አርባ እግሮች እንዲኖሩአቸው አድርግ። 22በድንኳኑ በስተ ጀርባ ባለው በምዕራብ በኩል፥ ስድስት ተራዳዎችን አድርግ። 23ለማእዘኖቹም ሁለት ተራዳዎች አድርግ። 24እነዚህ በማእዘኖቹ ላይ ያሉት ተራዳዎች ከታች በኩል ተጣምረው እስከ ላይ አንደኛው ዋልታ መያያዝ አለባቸው፤ ሁለቱን ማእዘኖች የሚያገናኙት ሁለት ተራዳዎች በዚሁ ዐይነት ይሠሩ። 25በዚህ ዐይነት በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት እግር ሆኖ ዐሥራ ስድስት የብር እግሮች ያሉአቸው ስምንት ተራዳዎች ይኖራሉ።
26“ዐሥራ አምስት መወርወሪያዎች ከግራር እንጨት ሥራ፤ ከእነርሱም አምስቱ ከድንኳኑ በአንድ ጐን ላሉት ተራዳዎች 27አምስቱም በሌላው ጐን ላሉት ተራዳዎች የቀሩት አምስቱ ደግሞ በስተ ምዕራብ ከኋላ በኩል ላሉት ተራዳዎች ይሆናሉ። 28መካከለኛውም መወርወሪያ በተራዳዎች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29ተራዳዎችንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ለመወርወሪያዎቹም መያዣ እንዲሆኑ የወርቅ ዋልታዎች አብጅላቸው፤ መወርወሪያዎቹም በወርቅ የተለበጡ ይሁኑ፤ 30ድንኳኑን በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት ትከል።
31“ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃን ሥራ፤ በእርሱም ላይ ኪሩቤል፥ በጥልፍ ጥበብ እንዲሳሉ አድርግ። 32እርሱንም ከግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ በተለበጡት፥ ኩላቦችና አራት የብር እግሮች ባሉአቸው ምሰሶዎች ላይ ስቀለው። 33መጋረጃውንም በድንኳኑ ጣራ ላይ በተርታ በተደረደሩት መያዣዎች ሥር ታንጠለጥለዋለህ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች የያዘውንም የቃል ኪዳን ታቦት ከመጋረጃው በስተኋላ በኩል ታኖረዋለህ፤ በዚህ ዐይነት መጋረጃው ቅድስት የተባለውን ስፍራ ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል፤ #ዕብ. 6፥19፤ 9፥3-5። 34ከዚህ በኋላ የቃል ኪዳኑን ታቦት በስርየት መክደኛው ክደነው፤ 35ጠረጴዛውን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ውጪ፥ ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል አኑር፤ መቅረዙንም በደቡብ በኩል አኑር።
36“ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ በጥልፍ ያጌጠ መጋረጃ አድርግለት። 37ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶዎችን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ ለእነዚህ ምሰሶዎች ከነሐስ የተሠሩ አምስት እግሮች አብጅላቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 26: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997