መጽሐፈ መሳፍንት 16
16
ሶምሶን በጋዛ
1አንድ ቀን ሶምሶን የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደሆነችው ወደ ጋዛ ሄደ፤ እዚያም አንዲት አመንዝራ ሴት አይቶ ከእርስዋ ጋር ለማደር ወደ ቤትዋ ገባ፤ 2የጋዛም ሰዎች ሶምሶን በዚያ መኖሩን ሰምተው ያንን ቦታ በመክበብ በከተማይቱ በር ሌሊቱን ሙሉ ሲጠብቁት ዐደሩ፤ “እስኪነጋ ጠብቀን እንገድለዋለን” ብለው በማሰብ ሌሊቱን ሙሉ አደፈጡ፤ 3ነገር ግን ሶምሶን ከሴቲቱ ጋር ተኝቶ የቈየው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ከዚያን በኋላ ከመኝታው ተነሣ፤ የከተማይቱን ቅጽር በር፥ ሁለቱን ምሶሶዎችና መቈለፊያዎቹን ሁሉ ፈነቃቀለ፤ ያንን ሁሉ በትከሻው ተሸክሞ ከኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኮረብታ ድረስ ወሰደ።
ሶምሶንና ደሊላ
4ከዚህ በኋላ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር ደሊላ ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ወደደ፤ 5የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ወደ እርስዋ ሄደው እንዲህ አሉአት፤ “ሶምሶንን አግባብተሽ ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘው ከምን እንደ ሆነና እንዴትስ አስረን በቊጥጥራችን ሥር በማድረግ ልናሸንፈው እንደምንችል ጠይቂው፤ እያንዳንዳችንም አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር እንሰጥሻለን።”
6ስለዚህ ደሊላ ሶምሶንን “ይህን ያኽል ብርቱ የሚያደርግህ ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ፤ አንድ ሰው አንተን አስሮ ሊያደክምህ የሚችለው እንዴት ነው?” አለችው።
7ሶምሶንም “እርጥብ በሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮች ቢያስሩኝ እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።
8ከዚህ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች እርጥብ የሆኑ ሰባት አዳዲስ ጠፍሮችን ለደሊላ ይዘውላት መጡ፤ እርስዋም በእርሱ ሶምሶንን አሰረችው። 9በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ፈትል እሳት ሲነካው እንደሚበጣጠስ ጠፍሮቹን በጣጠሳቸው፤ ስለዚህ አሁንም ብርታት የሚያገኝበትን ምሥጢር ገና አልደረሱበትም ነበር።
10ደሊላም ሶምሶንን “እነሆ! አታለልከኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ!” አለችው።
11እርሱም “ሥራ ባልተሠራበት አዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” ሲል መለሰላት።
12ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ አሰረችው፤ በሌላ ክፍል ሆነው የሚጠባበቁ ወንዶች ስለ ነበሩ እርሷ “ሶምሶን፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” ስትል ጮኸች፤ እርሱ ግን ገመዱን ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው።
13ደሊላም ሶምሶንን “እስከ አሁን ድረስ አሞኘኸኝ፤ እውነቱንም አልነገርከኝም፤ አሁንም አንተን እንዴት ማሰር እንደሚቻል እባክህ ንገረኝ” አለችው።
እርሱም “የራሴን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ብትጐነጒኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ” አላት።
14ከዚህ በኋላ ደሊላ ተኝቶ ሳለ የራሱን ጠጒር ሰባቱን ቁንዳላዎች ከድር ጋር ጐንጒና በችካል ቸከለችው፤ ከዚያ በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” ብላ ጮኸች፤ እርሱ ግን ከእንቅልፉ ነቅቶ ጠጒሩን ከችካሉና ከድሩ ላይ ነቀለው።
15ስለዚህ እርስዋ “ልብህ ከእኔ ጋር ሳይሆን እንዴት እወድሻለሁ ትለኛለህ? ሦስት ጊዜ አታለልከኝ፤ እስከ አሁንም ይህን ሁሉ ብርታት ያገኘኸው ከምን እንደ ሆነ አልነገርከኝም” አለችው። 16ዕለት ዕለትም እየነዘነዘች ሞቱን እስከሚመኝ ድረስ አስጨነቀችው፤ 17በመጨረሻ እውነቱን ነገራት፤ እንዲህም አላት፦ “ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየሁ ስለ ሆነ ጠጒሬ ተላጭቶ አያውቅም፤ ጠጒሬ ቢላጭ ግን ኀይል ተለይቶኝ እንደማንኛውም ሰው ደካማ እሆናለሁ።”
18ደሊላ እውነቱን እንደ ነገራት በተረዳች ጊዜ “እውነቱን ስለ ነገረኝ አንድ ጊዜ ተመልሳችሁ ኑ” ስትል ወደ ፍልስጥኤማውያን ገዢዎች መልእክት ላከች። እነርሱም ብሩን ይዘው መጡ። 19ደሊላ ሶምሶንን በጭንዋ ላይ አስተኝታ፤ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገች። አንድ ሰውም ጠርታ ሰባቱን የጠጒሩን ቁንዳላዎች እንዲቈረጡ አደረገች፤ ኀይሉም ከእርሱ ተለይቶት ስለ ነበር በማዋረድ ታስጨንቀው ነበር፤ 20ከዚያም በኋላ “ሶምሶን! ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው፤ እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ “እንደ ወትሮው በጣጥሼ እሄዳለሁ” ብሎ አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተለየው አላወቀም ነበር፤ 21ፍልስጥኤማውያንም ከማረኩት በኋላ ሁለቱን ዐይኖቹን አወጡ፤ ወደ ጋዛም ወስደው በነሐስ ሰንሰለት በማሰር በታሰረበት ቤት እህል እንዲፈጭ አደረጉት፤ 22የተቈረጠውም የራሱ ጠጒር እንደገና ማደግ ጀመረ።
የሶምሶን አሟሟት
23“በጠላታችን በሶምሶን ላይ ድልን እንድንቀዳጅ አድርጎናል” ብለው የደስታ በዓል ለማዘጋጀትና ለአምላካቸውም ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች በአንድነት ተሰበሰቡ፤ 24እርሱንም ባዩት ጊዜ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን ለእኛ አሳልፎ ሰጠን” እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ 25ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ እንዲጫወትልን ሶምሶንን ጥሩት አሉ ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፤ በፊታቸውም ተጫወተ፤ በምሰሶና በምሰሶ መካከል አቆሙት። 26ሶምሶንም እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፥ “ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ምሰሶዎች አስጨብጠኝና እነርሱን ተደግፌ ልቁም” አለው። 27በሕንጻውም ውስጥ ብዙ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም የፍልስጥኤም ገዢዎች ሁሉ ነበሩ፤ በሰገነት ላይ ሆነው ሶምሶን ሲያጫውታቸው የሚመለከቱ ሦስት ሺህ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ።
28ከዚህ በኋላ ሶምሶን “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ አስበኝ፤ አምላኬ ሆይ! እባክህ ኀይል ስጠኝና ፍልስጥኤማውያን ዐይኖቼን ስላወጡ አንድ ጊዜ ብቻ እንድበቀላቸው አድርገኝ!” ብሎ ጸለየ። 29ስለዚህ ሶምሶን ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ሁለቱን መካከለኛ ምሰሶዎች ጨበጠ፤ በቀኝ እጁ አንዱን ምሰሶ፥ በግራ እጁም ሌላውን ምሰሶ ይዞ ተጠጋ፤ 30“ሕይወቴ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ትለፍ!” ብሎ ጮኸ፤ በሙሉ ኀይሉም በገፋቸው ጊዜ ሕንጻው በፍልስጥኤም ገዢዎቹና እዚያ ባሉት ሁሉ ላይ ተደረመሰ፤ ሶምሶንም በሕይወቱ ሳለ ከገደላቸው ይልቅ በሞተበት ጊዜ የገደላቸው በዙ።
31ወንድሞቹና የቀሩት ቤተሰቡ ሁሉ መጥተው አስከሬኑን ወሰዱት፤ ወስደውም በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል በሚገኘው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት፤ ሶምሶን ኻያ ዓመት ሙሉ እስራኤልን መራ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997