ትንቢተ ኤርምያስ 21
21
ስለ ኢየሩሳሌም ድል መሆን የተነገረ ትንቢት
1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ፓሽሑርንና የመዕሤያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እኔ ልኮ እንዲህ ሲል አስጠየቀኝ፦ 2“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከነሠራዊቱ ከተማይቱን ለመውጋት በመክበብ ላይ ይገኛል፤ ስለዚህ ምናልባት በረድኤት ከእኛ ጋር ሆኖ ድንቅ ሥራውን በመግለጥ ናቡከደነፆርን እንዲመለስ ያደርግልን እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ጠይቅልን።” #2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21።
3በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ቃሉን ስለ ነገረኝ ወደ እኔ ተልከው የመጡትን ሰዎች ለሴዴቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት አልኳቸው፥ 4“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል፤ ‘ሴዴቅያስ ሆ! ከቅጽርህ በስተውጪ በኩል ከበባ ያደረጉብህን የባቢሎንን ንጉሥና ባቢሎናውያንን የምትዋጋበት የጦር መሣሪያ አንተን ተመልሶ እንዲያጠቃ አደርጋለሁ፤ የጦር መሣሪያውንም በከተማይቱ መካከል እንዲከመር አደርጋለሁ። 5እኔ ራሴ በሚነድ ቊጣ፥ በታላቅ ተግሣጽ በኀይሌና በሥልጣኔ አንተን እዋጋለሁ። #ማቴ. 23፥38፤ ሉቃ. 13፥35። 6በዚህች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ እመታለሁ፤ ሰዎችና እንስሶች በአንድነት በአሠቃቂ ወረርሽኝ ያልቃሉ፤ 7አንተና መኳንንትህ ከወረርሽኝ፥ ከጦርነትና ከራብ የሚተርፉትንም ሕዝብ በሙሉ በንጉሥ ናቡከደነፆርና ሊገድሉህ በሚፈልጉህ ጠላቶችህ እንድትማረኩ አደርጋለሁ፤ እርሱም ምሕረት ወይም ርኅራኄ በማሳየት አንድ ሰው እንኳ አይተውልህም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብዬ እንድናገር አዘዘኝ፦ “እነሆ አድምጡ! እኔ እግዚአብሔር ወደ ሕይወት የሚወስደውንና ወደ ሞት የሚያደርሰውን መንገድ በፊታችሁ አኑሬአለሁ፤ ከሁለቱ አንዱን ምረጡ፤ 9በዚህች ከተማ የሚቀሩ ሁሉ በጦርነት ወይም በራብ፥ ወይም በወረርሽኝ ይሞታሉ፤ አሁን ከተማይቱን ከበው ወዳሉት ወደ ባቢሎናውያን ሄዶ እጁን የሚሰጥ ግን አይሞትም፤ ሌላው ቢቀር ሕይወቱን ያተርፋል፤ 10ይህች ከተማ እንድትጠፋ ወስኛለሁ፤ ፈጽሞም ምሕረት አላደርግላትም፤ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
በይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ ላይ የተሰጠ ፍርድ
11-12የዳዊት ዘሮች ለሆኑት ለይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ እንድነግራቸው እግዚአብሔር የሰጠኝ ቃል ይህ ነው፦ “እኔ እግዚአብሔር የምነግራችሁን አድምጡ፤ በየማለዳው ፍትሕ እንዳይጓደል አድርጉ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራበት ጠብቁ፤ ይህን ባታደርጉ ግን ከምትሠሩት ክፋት የተነሣ ቊጣዬ እንደ እሳት ይነዳል፤ ሊያጠፋውም የሚችል አይኖርም፤ #2ነገ. 23፥31-34፤ 2ዜ.መ. 36፥1-4። 13አንቺም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በሜዳ ላይ እንደሚገኝ ቋጥኝ ከሸለቆዎች በላይ ከፍ ብለሽ ትታዪአለሽ፤ ነገር ግን እኔ እዋጋሻለሁ፤ አንቺ ግን ማንም የሚደፍርሽና ምሽጎችሽን ጥሶ የሚገባ ያለ አይመስልሽም፤ 14ነገር ግን ስላደረግሽው ነገር ሁሉ እኔ እቀጣሻለሁ፤ ቤተ መንግሥትሽ በእሳት እንዲቃጠል አደርጋለሁ፤ ያም እሳት በዙሪያው የሚገኘውን ነገር ሁሉ ያጋያል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 21: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997