ትንቢተ ኤርምያስ 22
22
ኤርምያስ ለይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ የተናገረው ቃል
1-2እግዚአብሔር የዳዊት ዘር ወደ ሆነው ወደ ይሁዳ ቤተ መንግሥት እንድወርድና በዚያም ለንጉሡ፥ ለመኳንንቱና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እኔ የምነግራቸውን ቃል እንዲያዳምጡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለኝ፦ 3“እኔ እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድና እውነት የሆነውን ነገር እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራ ጠብቁ፤ መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አታንገላቱ፤ በዚህም በተቀደሰ ስፍራ የንጹሕ ሰው ደም አታፍስሱበት። 4ልክ እኔ እንዳዘዝኳቸው ብታደርጉ፥ የዳዊት ዘሮች ከዙፋናቸው አይወርዱም፤ እንደ ወትሮው ሁሉ ከመኳንንቱና ከሕዝቡ ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ላይ በመቀመጥ በዚህ ቤተ መንግሥት የቅጽር በሮች መግባት ትችላላችሁ። 5ትእዛዜን የማትፈጽሙ ከሆነ ግን ይህ ቤተ መቅደስ ፈራርሶ እንደሚወድቅ በራሴ በመማል አረጋግጥላችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
6“የይሁዳ ነገሥታት ቤተ መንግሥት የገለዓድን አገርና የሊባኖስን ተራራዎች ያኽል ለእኔ የተዋበ ነው፤ ነገር ግን ማንም የማይኖርበት ባድማ አደርገዋለሁ። 7እርሱን የሚያፈራርሱ ሰዎችን እልካለሁ፤ እነርሱም መጥረቢያቸውን ይዘው ይመጣሉ፤ ከተዋበ የሊባኖስ ዛፍ የተሠሩትንም ዐምዶች ቈራርጠው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል።
8“ከዚያን በኋላ በዚያ በኩል የሚያልፉ ብዙ የውጪ አገር ሰዎች ‘በዚህች በታላቅ ከተማ ላይ እግዚአብሔር ይህን ጥፋት ያመጣው ለምን ይሆን?’ በማለት እርስ በርሳቸው ይጠያየቃሉ። 9እናንተ ከእኔ ከአምላካችሁ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችሁ ባዕዳን አማልክትን በማምለካችሁና በማገልገላችሁ ምክንያት መሆኑንም ይረዳሉ።”
ኤርምያስ ስለ ሻሉም የተናገረው ቃል
10የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ስለ ንጉሥ ኢዮስያስ አታልቅሱ፤
በመሞቱም አትዘኑ፤
ነገር ግን የኢዮስያስ ልጅ ሻሉም፤
ዳግመኛ ወደማይመለስበት ቦታ ስለሚወሰድ፥
የትውልድ አገሩንም ዳግመኛ ስለማያይ፥
ለእርሱ ምርር ብላችሁ አልቅሱ።
11በአባቱ ምትክ በይሁዳ ስለ ነገሠው ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሻሉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዳግመኛ ወደማይመለስበት ወደ ሩቅ አገር ይሄዳል፤ 12በዚያም ተማርኮ በተወሰደበት አገር ስለሚሞት ዳግመኛ ተመልሶ ይህችን ምድር አያይም።”
ኤርምያስ ስለ ንጉሥ ኢዮአቄም የተናገረው ቃል
13ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዐመፅ ለሠራተኞች የድካማቸውን ዋጋ ሳይከፍል ለሚያሠራ ሰው ወዮለት!
14ይህ ሰው “ለራሴ ትልቅ ቤት ከሰፊ ሰገነት ጋር እሠራለሁ፤ እንዲሁም ሰፋፊ መስኮቶችን አወጣለታለሁ፤ ቤቱን በሰፋፊ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት አስጌጠዋለሁ፤ ደማቅ ቀይ ቀለምም እቀባዋለሁ” ይላል።
15ሌሎች ሰዎች ከሚያደርጉት ይበልጥ
ምርጥ በሆነ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤትህን በመሥራትህ
የተሻልክ ንጉሥ የሆንክ ይመስልሃልን?
አባትህ ደስታ የሞላበት ሙሉ ዕድሜ ነበረው፤
እርሱ ዘወትር ትክክለኛና ቅን ከመሆኑ የተነሣ
የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር።
16ለድኾች በቅንነት ስለሚፈርድ፥
ሁሉ ነገር ይሳካለት ነበር፤
እግዚአብሔርን ማወቅ ይሉሃል ይህ ነው።
17የአንተ ሥራ ንጹሕ ደምን ማፍሰስና ሰውን መጨቈን ነው፤
ዐይንህና ልብህም የሚያተኲሩት
አጭበርብሮ ትርፍን በማግበስበስ ላይ ብቻ ነው።
18ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም የሚለው ይህ ነው፥
“እርሱ በሚሞትበት ጊዜ
‘ዋይ! ወዮ! ወንድሜ ሆይ!’ እያሉ በማልቀስ አያዝኑለትም፤
እንዲሁም ‘ጌታዬ ሆይ! ንጉሤ ሆይ! ወዮ!’ እያለ የሚያለቅስለት አይኖርም። #2ነገ. 23፥36—24፥6፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7።
19ሬሳውም ክብር አጥቶ እየተጐተተ፥
ከኢየሩሳሌም ቅጽር በር ውጪ ተጥሎ
የአህያ አቀባበር ይቀበራል።”
ኢየሩሳሌም ስለሚገጥማት ችግር ኤርምያስ የተናገረው ቃል
20የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የጦር ጓደኞቻችሁ ሁሉ ስለ ተሸነፉ
ወደ ሊባኖስ ሂዱና ጩኹ፤
ወደ ባሳን ምድርም ሄዳችሁ አልቅሱ፤
በሞአብ ተራራዎች ላይ ሆናችሁም ተጣሩ።
21በብልጽግና በምትኖሩበት ጊዜ እግዚአብሔር ተናገራችሁ፤
እናንተ ግን ማዳመጥ እምቢ አላችሁ፤
ከመጀመሪያ ጀምሮ የምታደርጉት ይህንኑ ነው።
እግዚአብሔርንም መታዘዝ እምቢ አላችሁ።
22በምትሠሩት ኃጢአት ምክንያት
ነፋስ ገለባን ጠራርጎ እንደሚወስድ፥
መሪዎቻችሁ ተጠራርገው ይወሰዳሉ።
የተማመናችሁባቸው የጦር ጓደኞቻችሁም ተማርከው ወደ ባዕድ ሀገር ይወሰዳሉ፤
ኀፍረትና ውርደትም ይደርስባችኋል።
23አሁንማ ከሊባኖስ መጥቶ በተሠራ የሊባኖስ እንጨት ውስጥ በሰላም ዐርፋችሁ ትኖራላችሁ፤
ነገር ግን እንደ ወላድ ሴት የምጥ ጣዕር ሲይዛችሁ ምን ይበጃችሁ ይሆን?
በዮአኪን ላይ የደረሰ የእግዚአብሔር ፍርድ
24ለኢዮአቄም ልጅ ለኢኮንያን እግዚአብሔር እንዲህ አለው፦ “እኔ ሕያው አምላክ አንተ በቀኝ እጄ እንደሚገኝ የማኅተም ቀለበት ብትሆን እንኳ አውልቄ እጥልሃለሁ፤ #2ነገ. 24፥8-15፤ 2ዜ.መ. 36፥9-10። 25ሊገድሉህ ለሚፈልጉና አንተም እጅግ ለምትፈራቸው ሕዝብ፥ ማለትም ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ለባቢሎናውያን አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ 26አንተንም፥ የወለደችህ እናትህንም እንድትሰደዱ አደርጋለሁ፤ ማንኛችሁም ወዳልተወለዳችሁበት አገር ሄዳችሁ ሁላችሁም እዚያ ትሞታላችሁ። 27ይህችን አገር እንደገና ለማየት ትናፍቃለህ፤ ነገር ግን ዳግመኛ አትመለስባትም።”
28እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ንጉሥ ኢኮንያን ከተጣለ በኋላ ማንም እንደማይፈልገው ሰባራ ገንቦ መሆኑ ነውን? እርሱና ልጆቹ ተማርከው ወደማያውቁት አገር የተወሰዱት ለምንድን ነው?”
29ምድር፥ ምድር፥ ምድር ሆይ!
እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እነሆ አድምጪ!
30“ይህ ሰው ልጆቹን ሁሉ አጥቶ
ኑሮው የማይሳካለት እንዲሆን ተፈርዶበታል፤
የዳዊትን ዙፋን ለመውረስ
በይሁዳ የሚነግሡ ዘሮች አይተርፉለትም ብለሽ መዝግቢ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 22: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997