የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 16

16
ተአምር ለማየት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 8፥11-13ሉቃ. 12፥54-56)
1ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው “ከሰማይ ተአምር አሳየን” ሲሉ ጠየቁት። #ማቴ. 12፥38፤ ሉቃ. 11፥16። 2እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ [“በማታ ሰማይ ቀልቶ ስታዩ ‘ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤ 3ሲነጋ በጠዋት ደግሞ ‘ሰማዩ ደመና ሆኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል’ ትላላችሁ፤ የሰማዩንስ መልክ መለየት ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም።] #16፥3 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች በቊ. 2 እና 3 ያለውን የኢየሱስን አባባል አይጠቅሱም። 4ክፉና የማያምን ትውልድ፥ ምልክት ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ትቶአቸው ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። #ማቴ. 12፥39፤ ሉቃ. 11፥29።
የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን እርሾ
(ማር. 8፥14-21)
5ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ማዶ በተሻገሩ ጊዜ ረስተው እንጀራ አልያዙም ነበር፤ 6ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ልብ አድርጉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” አላቸው። #ሉቃ. 12፥1።
7እነርሱም “ይህን ማለቱ ምናልባት እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” በማለት እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
8ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ‘እንጀራ ስላልያዝን ነው’ ብላችሁ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? 9ገና የማታስተውሉ ናችሁን? አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? #ማቴ. 14፥17-21። 10እንዲሁም ሰባት እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው እንደበቃና የተረፈውን ፍርፋሪ ምን ያኽል መሶብ ሙሉ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን? #ማቴ. 15፥34-38። 11እንግዲህ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ!’ ብዬ ስነግራችሁ ስለ እንጀራ አለመሆኑን እንዴት አታስተውሉም?”
12ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ተጠንቀቁ ያላቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዳልሆነ ተገነዘቡ።
ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ
(ማር. 8፥27-30ሉቃ. 9፥18-21)
13ኢየሱስ የፊልጶስ ቂሳርያ ወደሚባል ክፍለ ሀገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው።
14እነርሱም “አንዳንዶች ‘መጥምቁ ዮሐንስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ‘ኤልያስ ነው’ ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ‘ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ይላሉ” አሉት። #ማቴ. 14፥1-2፤ ማር. 6፥14-15፤ ሉቃ. 9፥7-8።
15ኢየሱስም “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው።
16በዚያን ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፦ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። #ዮሐ. 6፥66-69።
17ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! የተባረክህ ነህ! ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሰው አይደለም። 18እኔም እንዲህ እልሃለሁ፤ አንተ (ጴጥሮስ)፥ አለት ነህ፤ በዚህችም የመሠረት ድንጋይ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ ይህችንም ቤተ ክርስቲያን የሞት ኀይል እንኳ አያሸንፋትም። 19እነሆ፥ ለአንተ የሰማይ መንግሥትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” #ማቴ. 18፥18፤ ዮሐ. 20፥23። 20ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
ኢየሱስ ስለሚደርስበት መከራና ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተናገረ
(ማር. 8፥31-33ሉቃ. 9፥22-27)
21ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አለብኝ፤ እዚያም ከሽማግሌዎች፥ ከካህናት አለቆችና ከሕግ መምህራን መከራ ይደርስብኛል፤ ይገድሉኛል፤ ግን በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ።”
22ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ለብቻ ገለል አድርጎ፦ “ጌታ ሆይ! ከቶ አይሆንም! ይህ ነገር ከቶ አይደርስብህም!” እያለ ይገሥጸው ጀመር።
23ኢየሱስ ግን ዞር ብሎ ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን! ከኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር ስለማታስብ ለእኔ እንቅፋት ነህ” አለው።
ክርስቶስን መከተል የሚጠይቀው መሥዋዕትነት
(ማር. 8፥34—9፥1ሉቃ. 9፥23-27)
24ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “እኔን መከተል የሚፈልግ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። #ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27። 25ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ግን ያገኛታል። #ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25። 26ሰው የዓለሙን ሁሉ ሀብት ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ፥ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? 27የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሆኖ ከመላእክቱ ጋር ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይከፍለዋል። #ማቴ. 25፥31፤ መዝ. 62፥12፤ ሮም 2፥6። 28በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ክብር ሲመጣ እስከሚያዩ ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል የማይሞቱ ሰዎች አሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ