የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 39

39
ለክህነት የሚሆኑ ልብሶች አሠራር
1በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ በብልሃት የተሠራ ልብስ አደረጉ፥ ጌታም ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ።
2ኤፉዱንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራ። 3ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቆረጡት። ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራው በሰማያዊው፥ በሐምራዊው፥ በቀዩ ግምጃ፥ በተፈተለው ጥሩ በፍታ መካከል በእርሱ ጠለፉ። 4እንዲጋጠም በሁለቱ ትከሻዎች ላይ መጋጠሚያ ሠሩለት፥ በሁለቱ ጫፎች እንዲጋጠም አደረጉት። 5በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ፥ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከእርሱ ጋር ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር።
6በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። 7ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች እንዲሆኑ በኤፉዱ በትከሻው ላይ አደረጋቸው።
8የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠራው። 9አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱንም ኪስ ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ አንድ ስንዝር፥ ወርዱም አንድ ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። 10በእርሱም ላይ በአራት ረድፍ ዕንቁዎቹን አደረጉበት፤ በመጀመሪያ ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ 11በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና አልማዝ፤ 12በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፤ 13በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ። 14የዕንቁዎቹም ድንጋዮች እንደ ዐሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፥ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። 15ለደረቱ ኪስም እንደ ገመድ የተጐነጐኑ ድሪዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ። 16ሁለት የወርቅ ፈርጦችና ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ በኩል አደረጉት። 17ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ጫፎች ባሉት በሁለቱ ቀለበቶች አስገቡ። 18የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ። 19ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው። 20ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከትከሻዎቹ በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው። 21ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሰሩት።
22የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ሠራው። 23በቀሚሱ መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም አንገትጌው ዙሪያውን ተጠልፎ ነበር። 24በቀሚሱ ታችኛው ዘርፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ በፍታ ሮማኖችን አደረጉ። 25ከንጹሕ ወርቅ ሻኩራዎችን ሠሩ፥ ሻኩራዎቹንም በሮማኖቹ መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። 26ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ለማገልገል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኩራና ሮማን፥ ሻኩራና ሮማን አደረጉ።
27የሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ቀሚስ አዘጋጁ፥ 28ከጥሩ በፍታ መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም ቆቦች፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ፥ 29ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተጠለፈ መታጠቂያ ሠሩ።
30የተቀደሰውን አክሊል አበባ ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም “ለጌታ የተቀደሰ” የሚል ጽሑፍ ቀረጹበት። 31ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው በመጠምጠሚያው ላይ እንዲያንጠለጥሉት ሰማያዊ ፈትል አሰሩበት።
የሥራው ፍጻሜ
32የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጠናቀቀ። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ፤ እንዲሁ አደረጉ። 33ማደሪያውን ወደ ሙሴ አመጡት፥ ድንኳኑን፥ የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ፥ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንና እግሮቹን፥ 34ከቀይ አውራ በግ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበት የተሠራ መደረቢያ፥ መሸፈኛ መጋረጃ፥ 35የምስክሩን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውን፥ 36ገበታውንና ዕቃውን ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹን፥ 37ንጹሑን መቅረዝ፥ መብራቶቹን፥ የተደረደሩትን ቀንዲሎችና ዕቃዎቻቸውን ሁሉ፥ የመብራቱን ዘይት፥ 38የወርቁን መሠዊያ፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፥ የድንኳኑን ደጃፍ መጋረጃ፥ 39የናሱን መሠዊያ፥ የናሱን መከታ፥ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫው፥ 40የአደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹን፥ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹን፥ ካስማዎቹን፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ 41በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም እንዲያገለግሉበት የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶችና የልጆቹን ልብሶች አመጡ። 42የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ ልክ እንደዛው አድርገው ሠሩ። 43ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆ ልክ ጌታ እንዳዘዘው አድርገውት ነበር፤ እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ