ትንቢተ ኤርምያስ 21
21
ስለ ኢየሩሳሌም መያዝ የተነገረ ትንቢት
1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና የካህኑን የመዕሴይን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፦ እንዲህም አለ፦ 2“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋን ዘንድ መጥቶአልና ከእኛ ይመለስ ዘንድ፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ እንደ ሆነ ስለ እኛ፥ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅ።” 3ኤርምያስም እንዲህ አላቸው፥ “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ 4የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን የጦር መሣሪያችሁን እሰጣችኋለሁ፤ እነዚያንም በዚህች ከተማ መካከል እሰበስባቸዋለሁ። 5እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቍጣና በመዓት፥ በታላቅም መቅሠፍት አወጋችኋለሁ። 6በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፤ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ። 7ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና አገልጋዮቹን፥ ከቸነፈርና ከሰይፍ፥ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትን ሕዝቡንም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውም።”
8ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ። 9በዚህች ከተማ ውስጥ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፤ ሰውነቱም ምርኮ ትሆናለች። 10ለመልካም ሳይሆን ለክፉ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።”
11የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 12የዳዊት ቤት ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይነድድና ማንም ሳያጠፋው እንዳያቃጥል፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ፤ የተነጠቀውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ። 13እነሆ በሜዳ ላይ ባለው ድንጋያማ ሸለቆ የምትቀመጥ ሆይ! እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ እናንተም፦ የሚያስደነግጠን#ዕብ. “በእኛ ላይ የሚወርድ” ይላል። ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው? የምትሉ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤ 14እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር#“እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በዱርዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፤ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 21: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ