ኦሪት ዘጸአት 33
33
1-3እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ሂድ፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም፦ ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር፥ ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ምድር አንተ ከግብፅ ምድር ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህም ውጣ። አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንህ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ በአንተ መካከል አልወጣምና በፊትህ መልአክ እሰድዳለሁ፤ ከነዓናዊውን አሞራዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም አወጣልሃለሁ። 4ሕዝቡም ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው አዘኑ፤ ከእነርሱም ማንም ጌጡን አልለበሰም። 5እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ለእስራኤል ልጆች፦ እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፥ አንድ ጊዜ በእናንተ መካከል ብወጣ አጠፋችኋለሁ፤ አሁንም የማደርግባችሁን አውቅ ዘንድ ጌጣችሁን ከእናንተ አውጡ በላቸው አለው። 6የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወጡ። 7ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። 8ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። 9ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። 10ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። 11እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። 12ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፦ በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። 13አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። 14እግዚአብሔርም፦ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። 15እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። 16በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። 17እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው። 18እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። 19እግዚአብሔርም፦ እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። 20ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። 21እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ 22ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ 23እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 33: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ