ትንቢተ ሕዝቅኤል 42
42
1በውጭም አደባባይ በሰሜኑ መንገድ አወጣኝ፥ በልዩውም ስፍራ አንጻርና በሰሜን በኩል ባለው ግቢ ፊት ለፊት ወዳለው ዕቃ ቤት አገባኝ። 2መቶ ክንድ በሆነው ርዝመት ፊት በሰሜን በኩል መዝጊያ ነበረ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ። 3በውስጠኛውም አደባባይ በሀያው ክንድ አንጻር በውጭውም አደባባይ በወለሉ አንጻር በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ። 4በዕቃ ቤቶቹም ፊት በስተ ውስጥ ወርዱ አሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፥ መዝጊያዎቻቸውም ወደ ሰሜን ይመለከቱ ነበር። 5መተላለፊያውም አሳጥሮአቸዋልና ላይኞቹ ዕቃ ቤቶች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ። 6በሦስትም ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩላቸውምና ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ። 7በውጭ በዕቃ ቤቶቹ አጠገብ ያለው፥ ወደ ውጭው አደባባይ የሚመለከተው ቅጥር፥ በዕቃ ቤቶች ትይዩ የሆነ፥ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ነበረ። 8በመቅደሱ ፊት የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው መቶ ክንድ ሲሆን በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ነበረና። 9ከእነዚህም ዕቃ ቤቶች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባባት መግቢያ ነበረ። ይህም በቅጥሩ ራስ አጠገብ ነበረ።
10በደቡብም በኩል በልዩው ስፍራና በግቢው አንጻር ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 11በስተ ፊታቸውም የነበረ መንገድ በሰሜን በኩል እንደ ነበረው እንደ ዕቃ ቤቶቹ መንገድ ምስያ ነበረ። ርዝመታቸውም ወርዳቸውም መውጫቸውም ሥርዓታቸውም መዝጊያዎቻቸውም በዚያው ልክ ነበረ። 12በደቡብም በኩል ካሉት ዕቃ ቤቶች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ።
13እንዲህም አለኝ፦ በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቍርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ። 14ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፥ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፥ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ።
15ውስጠኛውንም ቤት ለክቶ በፈጸመ ጊዜ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ እርሱንም በዙሪያው ለካው። 16የምሥራቁን ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 17ዞረም፥ የሰሜኑንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 18ዞረም፥ የደቡቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 19ዞረም፥ የምዕራቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 20በአራቱ ወገን ለካው። የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ይለይ ዘንድ ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 42: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ