ትንቢተ ኤርምያስ 23
23
1የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር። 2ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፦ በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸውማል አልጐበኛችኋቸውምም፥ እነሆ፥ የሥራችሁን ክፋት እጐበኝባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 3የመንጋዬም ቅሬታ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ ወደ በረታቸው ሰብሰቤ እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ያፈራሉ ይበዙማል። 4የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፥ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፥ ከእነርሱም አንድ አይጐድልም፥ ይላል እግዚአብሔር።
5እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቍጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እርሱም እንደ ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል። 6በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ የሚጠራበትም ስም፦ እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው።
7ስለዚህ፥ እነሆ፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ 8ነገር ግን፦ የእስራኤልን ቤት ዘር ከሰሜን አገርና ካሰደድኋቸውም አገር ሁሉ ያወጣና የመራ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፥ በምድራቸውም ይቀመጣሉ።
9ስለ ነቢያት፥ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፥ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። 10ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፥ የምድረ በዳ ማሰማርያ ደርቆአል፥ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም። 11ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ድጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ፍግምግም ብለው ይወድቁባታል፥ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
13በሰማርያ ነቢያት ላይ ስንፍናን አይቻለሁ፥ በበኣል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤል ያስቱ ነበር። 14በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፥ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፥ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፥ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። 15ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።
16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፥ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፥ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። 17ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ እግዚአብሔር፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፥ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። 18ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?
19እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፍስ ወጥቶአል፥ የዓመፀኞችን ራስ ይገለባብጣል። 20የእግዚአብሔር ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፥ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ። 21እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፥ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። 22በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር።
23እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። 24ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር። 25አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። 26ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? 27አባቶቻቸው ስለ በኣል ስሜን እንደ ረሱ፥ እያንዳንዱ ለባልንጀራው በሚናገራት ሕልማቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። 28የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፥ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? 29በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር። 30ስለዚህ፥ እነሆ፥ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 31እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው፦ እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 32እነሆ፥ ሐሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም፥ ይላል እግዚአብሔር።
33ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችሁማለህ፥ ይላል እግዚአብሔር ትላቸዋለህ። 34የእግዚአብሔር ሸክም የሚለውን ነቢይንና ካህንን ሕዝቡንም ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። 35አንዱም አንዱ ለባልንጀራው፥ አንዱም አንዱ ለወንድሙ እንዲህ ይበል፦ እግዚአብሔር የመለሰው ምንድር ነው? እግዚአብሔርስ ምን ነገር ተናገረ? 36ለሰው ሁሉ ቃሉ ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፥ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን የሕያውን አምላክ ቃል ለውጣችኋልና። 37ለነቢዩ፦ እግዚአብሔር ምን መለሰልህ? እግዚአብሔርስ የተናገረው ምንድር ነው? ትላለህ። 38ነገር ግን፦ የእግዚአብሔር ሸክም ብትሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ፦ የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል፦ 39የእግዚአብሔር ሸክም ብላችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። 40የዘላለምንም ስድብ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘላለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 23: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ