ትንቢተ ኤርምያስ 24
24
1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ እግዚአብሔር አሳየኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። 2በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፥ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት። 3እግዚአብሔርም፦ ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ በለስን አያለሁ፥ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ።
4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጐነት እመለከተዋለሁ። 6ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፥ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
8እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌምን ቅሬታ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን እጥላቸዋለሁ። 9በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 10ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 24: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ