YouVersion Logo
Search Icon

1 ዮሐንስ 3

3
1የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው። 2ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት#3፥2 ወይም በሚታወቅበት ጊዜ ጊዜ እናየዋለን፤ እርሱን እንደምንመስልም እናውቃለን። 3በርሱ ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።
4ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው። 5እርሱ ኀጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በርሱም ኀጢአት የለም። 6በርሱም የሚኖር ኀጢአትን አያደርግም፤ ኀጢአት የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም አላወቀውም።
7ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 8ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው። 9ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን በመለማመድ አይቀጥልም፤ የርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደም ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም። 10የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።
እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ
11ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤ 12የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። 13ወንድሞች ሆይ#3፥13 ወንድሞች የሚለው የግሪኩ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አካል በመሆናቸው ያመኑትን ወንዶችንና ሴቶችንም ያመለክታል፤ ከዚህ ቍጥር ውጪ በ16 ላይ እናገኘዋለን።፤ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። 15ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።
16ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። 17ማንም የዚህ ዓለም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ልቡ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በርሱ ይኖራል? 18ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።
19እኛ ከእውነቱ መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፤ 20ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል። 21ወዳጆች ሆይ፤ ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤ 22ትእዛዞቹንም ስለምንጠብቅና በፊቱም ደስ የሚያሠኘውን ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከርሱ እንቀበላለን። 23ትእዛዙም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና እርሱ እንዳዘዘንም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው። 24ትእዛዞቹንም የሚጠብቁ ሁሉ በርሱ ይኖራሉ፤ እርሱም በእነርሱ ይኖራል። በእኛ መኖሩን በዚህ፣ ይኸውም እርሱ በሰጠን መንፈስ እናውቃለን።

Currently Selected:

1 ዮሐንስ 3: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in