YouVersion Logo
Search Icon

ቈላስይስ 2

2
1ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ስለማያውቁ ሁሉ ምን ያህል እየተጋደልሁ እንደ ሆነ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ 2ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጽግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤ 3የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነውና። 4ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ። 5ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋራ ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።
በክርስቶስ ያለ መንፈሳዊ ሙሉነት
6እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በርሱ ኑሩ፤ 7በርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።
8በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች#2፥8 መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።
9የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በርሱ ይኖራልና፤ 10እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። 11በርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን#2፥11 እንደዚህ ባለ ዐውድ ውስጥ ሥጋ የሚለው ቃል የሚያመላክተው ኀጢአተኛ የሆነውንና ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን መንፈስ የሚቃወመውን የሰው ማንነት ለማመላከት ነው። ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ 12በጥምቀትም ከርሱ ጋራ ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከርሱ ጋራ ደግሞ ተነሣችሁ።
13እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ#2፥13 አንዳንድ የጥንት ቅጆች አደረገን ይላሉ።፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ 14ሲቃወመንና ሲፃረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። 15የገዦችና የባለሥልጣናትንም ማዕርግ በመግፈፍ በመስቀሉ#2፥15 ወይም በርሱ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።
ከሰው ሥርዐት ነጻ መሆን
16እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ 17እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። 18ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ 19ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋራ ግንኙነት የለውም።
20ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? 21“አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ 22እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። 23እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።

Currently Selected:

ቈላስይስ 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in