YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 47

47
የባቢሎን ውድቀት
1“አንቺ የባቢሎን#47፥1 ወይም በዚህና በ5 ላይ ከለዳውያን ድንግል ልጅ ሆይ፤
ውረጂ፤ በትቢያ ላይ ተቀመጪ፤
አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤
ከዙፋንሽ ውረጂ፤ መሬት ላይ ተቀመጪ፤
ከእንግዲህ ውብ ወይም ለግላጋ፣
ተብለሽ አትጠሪም።
2ወፍጮ ወስደሽ እህል ፍጪ፤
መሸፋፈኛሽን አውልቂ፤
ቀሚስሽንም ከፍ ከፍ አድርጊ፤ ባትሽን ግለጪ፤
እየተንገዳገድሽ ወንዙን ተሻገሪ።
3ዕርቃንሽ ይገለጥ፤
ኀፍረትሽ ይታይ፤
እበቀላለሁ፤
እኔ ማንንም ሰው አልተውም።”
4የሚቤዠን የእስራኤል ቅዱስ፣
ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
5“አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤
ወደ ጨለማ ግቢ፤ ዝም ብለሽም ተቀመጪ፤
ከእንግዲህ የመንግሥታት እመቤት
ተብለሽ አትጠሪም።
6ሕዝቤን ተቈጥቼ ነበር፤
ርስቴን አርክሼው ነበር፤
አሳልፌ በእጅሽ ሰጠኋቸው፤
አንቺ ግን አልራራሽላቸውም፤
በዕድሜ በገፉት ላይ እንኳ፣
እጅግ ከባድ ቀንበር ጫንሽባቸው።
7አንቺም፣ ‘እስከ መጨረሻው፣
ለዘላለም ንግሥት እሆናለሁ!’ አልሽ፤
ሆኖም እነዚህን ነገሮች አላስተዋልሽም፤
ፍጻሜያቸው ምን እንደሚሆንም አላሰብሽም።
8“አሁንም አንቺ ቅምጥል ፍጡር፣
በራስሽ ተማምነሽ የምትቀመጪ፣
በልብሽም፣
‘እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ የለም፤
ከእንግዲህ መበለት አልሆንም፤
የወላድ መካንም አልሆንም’ የምትይ ስሚ!
9እነዚህ ሁለት ነገሮች፣
መበለትነትና የወላድ መካንነት፣
አንድ ቀን ድንገት ይመጡብሻል፤
የቱን ያህል አስማት፣
የቱንም ያህል መተት ቢኖርሽ፣
በሙሉ ኀይላቸው ይመጡብሻል።
10በክፋትሽ ተማምነሽ፣
‘ማንም አያየኝም’ አልሽ፤
ደግሞም፣ ‘እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ የለም’
ባልሽ ጊዜ፣
ጥበብሽና ዕውቀትሽ አሳሳቱሽ።
11ጥፋት ይመጣብሻል፤
ነገር ግን በአስማትሽ እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤
ወጆ ከፍለሽ ለማስወገድ የማትችዪው፣
ጕዳት ይወድቅብሻል፤
ያላሰብሽው አደጋ፣
ድንገት ይደርስብሻል።
12“በይ እንግዲህ፣ ከልጅነትሽ ጀምሮ የደከምሽባቸውን፣
አስማቶችሽን፣
ብዙ መተቶችን ቀጥዪባቸው፤
ምናልባት ይሳካልሽ፣
ምናልባትም ጠላቶችሽን ታሸብሪባቸው ይሆናል።
13የተቀበልሽው ምክር ሁሉ ድካም ብቻ ሆኖ አስቀርቶሻል!
እነዚያ ከወር እስከ ወር ከዋክብትን አንጋጦ በማየት የሚተነብዩ፣
ኮከብ ቈጣሪዎች እስኪ ይምጡ፤
ከሚደርስብሽም ነገር እስኪ ያድኑሽ።
14እነሆ፣ እነርሱ ገለባ ናቸው፤
እሳት ይበላቸዋል፤
ከነበልባሉ ወላፈን የተነሣ፣
ራሳቸውን ማዳን አይችሉም።
ሰው የሚሞቀው ፍም አይኖርም፤
ተቀምጠው የሚሞቁትም እሳት የለም።
15ከልጅነት ጀምሮ ዐብረሻቸው የደከምሽው፣
ዐብረሽ የተገበያየሻቸው፣
ሊያደርጉ የሚችሉት ይህንኑ ብቻ ነው።
እያንዳንዱ በስሕተቱ ይገፋበታል፤
አንቺን ግን የሚያድን የለም።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 47: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in