YouVersion Logo
Search Icon

ምሳሌ 27

27
1ነገ በሚሆነው አትመካ፤
ቀን የሚያመጣውን አታውቅምና።
2ሌላው ያመስግንህ እንጂ የገዛ አፍህ አይደለም፤
ሌላ ሰው ያወድስህ እንጂ የገዛ ከንፈርህ አይሁን።
3ድንጋይ ይከብዳል፤ አሸዋም ሸክም ነው፤
የቂል ሰው ቍጣ ግን ከሁለቱም ይከብዳል።
4ንዴት ጨካኝ፣ ቍጣም ጐርፍ ነው፤
በቅናት ፊት ግን ማን መቆም ይችላል?
5የተገለጠ ዘለፋ፣
ከተደበቀ ፍቅር ይሻላል።
6ከጠላት ደጋግሞ መሳም ይልቅ፣
የወዳጅ ማቍሰል ይታመናል።
7ለጠገበ ማር አይጥመውም፤
ለተራበ ግን እሬት እንኳ ይጣፍጠዋል።
8ከቤቱ ወጥቶ የሚባዝን ሰው፣
ጐጆዋን ለቅቃ እንደምትባዝን ወፍ ነው።
9ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤
የወዳጅ ማስደሰትም ከቅን ምክሩ ይመነጫል።
10የራስህንም ሆነ የአባትህን ወዳጅ አትተው፤
መከራ በሚያጋጥምህ ጊዜ ወደ ወንድምህ ቤት አትሂድ፤
ሩቅ ካለ ወንድም ቅርብ ያለ ጎረቤት ይሻላል።
11ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሠኘው፤
ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ።
12አስተዋይ ክፉን አይቶ ራሱን ይሸሽጋል፤
አላዋቂዎች ግን በዚያው ይቀጥላሉ፤ ይቀጡበታልም።
13ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሆነውን ልብሱን ግፈፈው፤
ለባዕድ ሴት የተዋሰውን በቃሉ ዐግተው።
14ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ ባልንጀራውን በማለዳ ቢመርቅ፣
እንደ ርግማን ይቈጠራል።
15ጨቅጫቃ ሚስት፣
በዝናብ ቀን እንደሚወርድ የማያቋርጥ ጠፈጠፍ ናት፤
16እርሷን ለመግታት መሞከር፣ ነፋስን እንደ መግታት ወይም
ዘይትን በእጅ እንደ መጨበጥ ነው።
17ብረት ብረትን እንደሚስል፣
ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል።
18በለስን የሚንከባከብ ፍሬዋን ይበላል፤
ጌታውን የሚያገለግልም ክብርን ይጐናጸፋል።
19ውሃ ፊትን እንደሚያሳይ፣
የሰውም ልብ ማንነቱን ገልጾ ያሳያል።
20ሲኦልና የሙታን ዓለም#27፥20 ወይም ሞትና ጥፋት እንደማይጠግቡ ሁሉ፣
የሰውም ዐይን አይረካም።
21ብር በማቅለጫ፣ ወርቅም በከውር እንደሚፈተን፤
ሰውም በአንደበት ምስጋና ይፈተናል።
22ቂልን በሙቀጫ ብትወቅጠው፣
እንደ እህልም በዘነዘና ብታደቅቀው፣
ቂልነቱን ልታስወግድለት አትችልም።
23በጎችህ በምን ሁኔታ እንዳሉ ደኅና አድርገህ ዕወቅ፤
መንጋህንም ተንከባከብ፤
24ሀብት ለዘላለም አይኖርምና፤
ዘውድም ከትውልድ ወደ ትውልድ ጸንቶ አይኖርም።
25ደረቁ ሣር ተወግዶ፣ አዲሱ ብቅ ሲል፣
በየኰረብታው ላይ ያለው ሣር ተሰብስቦ ሲገባ፣
26ከበግ ጠቦቶች ልብስ ታገኛለህ፤
ፍየሎችም የዕርሻ መሬት መግዣ ይሆኑሃል።
27አንተንና ቤተ ሰብህን፣
ገረዶችህንም ጭምር ለመመገብ፣
የተትረፈረፈ የፍየል ወተት ይኖርሃል።

Currently Selected:

ምሳሌ 27: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in