YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 24

24
ጳውሎስ በአይሁድ መከሰሱ
1ከአምስት ቀን በኋላ የካህናት አለቃው ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ሄደ፤ እነርሱም ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ ቀርበው ጳውሎስን ከሰሱ፤ 2ጳውሎስ ተጠርቶ በመጣ ጊዜ፥ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን ጀመረ፤
“ክቡር ፊልክስ ሆይ! በአንተ አማካይነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ በመልካም አስተዳደርህም ለሕዝባችን መሻሻል ተገኝቶአል፤ 3እጅግ የተከበርክ ፊልክስ ይህን መልካም አድራጎትህን በየቦታውና በየጊዜው የምንቀበለው ከፍ ባለ ምስጋና ነው። 4አሁን ግን ጊዜህን ሳላባክን ባጭሩ የምነግርህን በቸርነትህ እንድትሰማን እለምንሃለሁ፤ 5ይህ ሰው መጥፎ በሽታ ሆኖብናል፤ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ላይ ሁከት ያስነሣል፤ ናዝራውያን ለሚባሉት መሪያቸው ነው። 6ቤተ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ይዘነዋል፤ [በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤ 7ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው። 8ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ፤] ይህን በእርሱ ላይ ያቀረብነውን ክስ ሁሉ እውነት መሆኑን አንተ ራስህ እርሱን መርምረህ ልታረጋግጥ ትችላለህ።” 9አይሁድ “ይህ ሁሉ ነገር እውነት ነው” እያሉ በክሱ ተስማሙ።
ጳውሎስ በፊልክስ ፊት የመከላከያ ንግግር ማድረጉ
10አገረ ገዥው ፊልክስ በእጁ ጠቅሶ ጳውሎስ እንዲናገር ፈቀደለት፤ ጳውሎስም እንዲህ ሲል መለሰ፤
“ለብዙ ዓመቶች የዚህ አገር ገዢ መሆንክን ስለማውቅ ለቀረበብኝ ክስ መከላከያዬን በአንተ ፊት ሳቀርብ በጣም ደስ እያለኝ ነው፤ 11ለመስገድ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄድኩ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይበልጥ አንተ ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤ 12በቤተ መቅደስም ሆነ በምኲራብ ወይም በከተማ ውስጥ ከማንም ጋር ስከራከር ወይም ሕዝቡን ለሁከት ሳነሣሣ አላገኙኝም፤ 13አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። 14ነገር ግን ይህን ልገልጥልህ እወዳለሁ፤ እነርሱ አዲስ መንገድ በሚሉት የሃይማኖት ክፍል እምነት የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕግና በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈውንም ሁሉ አምናለሁ። 15እነርሱም ተስፋ እንደሚያደርጉት እኔም ጻድቃንና ኃጥአን ከሞት እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አደርጋለሁ። 16ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ዘወትር እተጋለሁ።
17“ከኢየሩሳሌም ከወጣሁ ብዙ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ለወገኖቼ የሚሆን የእርዳታ ገንዘብና ለእግዚአብሔር የሚሰጥ መባ ይዤ መጣሁ። 18በቤተ መቅደስም ያገኙኝ ይህንኑ ሳደርግ ነው፤ በዚያን ጊዜ የመንጻትን ሥርዓት ፈጽሜ ነበር፤ ከእኔ ጋር ብዙ ሕዝብ አልነበረም፤ ሁከትም አልተነሣም። #ሐ.ሥ. 21፥17-28። 19ነገር ግን ከእስያ የመጡት አይሁድ እዚያ ነበሩ፤ እነርሱ በእኔ ላይ የክስ ምክንያት ካላቸው በአንተ ፊት ቀርበው ይናገሩ። 20ከዚህ በኋላ በሸንጎው ፊት በቀረብኩ ጊዜ ያደረግኹት በደል እንዳለ እነዚህ የቀረቡ ሰዎች ይናገሩ። 21እርግጥ በመካከላቸው ቆሜ ‘የሙታን ትንሣኤ አለ በማለቴ ዛሬ ለፍርድ በፊታችሁ ቀርቤአለሁ’ ብዬ ከፍ ባለ ድምፅ ተናግሬአለሁ፤ ከዚህ በቀር ሌላ ያደረግኹት ነገር የለም።” #ሐ.ሥ. 23፥6።
22ፊልክስ ግን ስለ ክርስትና እምነት በደንብ ያውቅ ስለ ነበር “የጦር አዛዡ ሉስዮስ በመጣ ጊዜ፥ ስለ ጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” ብሎ አሰናበታቸው። 23ጳውሎስን ይጠብቅ የነበረውንም መቶ አለቃ “እምብዛም ነጻነት ሳትከለክለው በጥንቃቄ ጠብቀው፤ ወዳጆቹም የሚያስፈልገውን ሁሉ ይዘውለት ሲመጡ አትከልክልበት” አለው።
ጳውሎስ በፊልክስና በድሩሲላ ፊት መቅረቡ
24ከጥቂት ቀኖች በኋላ ፊልክስ ዱሩሲላ ከተባለች አይሁዳዊት ሚስቱ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ማመን ሲናገር ሰማ። 25ጳውሎስ ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ፍርድ በተናገረ ጊዜ ፊልክስ ፈርቶ “አሁን ሂድ፤ ሲመቸኝ ሌላ ጊዜ አስጠራሃለሁ” አለው። 26ፊልክስ ከጳውሎስ ጉቦ ለመቀበል ተስፋ ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ ጳውሎስን እያስጠራ ያነጋግረው ነበር።
27ከሁለት ዓመት በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ቦታ ተተካ፤ ፊልክስ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ፈልጎ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for የሐዋርያት ሥራ 24