YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘዳግም 6

6
ታላቁ ትእዛዝ
1“አሁን ተሻግራችሁ በርስትነት በሚሰጣችሁ ምድር እንድትጠብቁት እግዚአብሔር አምላክህ እንዳስተምርህ ያዘዘኝ ትእዛዞች፥ ሕግና ሥርዓት እነዚህ ናቸው። 2በዚያች ምድር ለረጅም ዘመናት መኖር እንድትችሉ አንተና ልጆችህ፥ የልጅ ልጆችህም በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን መፍራትና እኔ ለሰጠኋችሁ ደንቦችና ትእዛዞች ታዛዦች መሆን ይገባችኋል። 3የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነዚህን ሕግጋት አድምጡ! ታዘዙላቸውም! ይህን ብታደርጉ ለቀድሞ አባቶቻችሁ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በማርና በወተት በበለጸገች በዚያች ለም ምድር ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንላችኋል፤ ትበዛላችሁም።
4“እስራኤል ሆይ! ይህን አስታውስ! እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ #ማር. 12፥29። 5እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤ #ማቴ. 22፥37፤ ማር. 12፥30፤ ሉቃ. 10፥27። 6ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች አትርሳ፤ 7እነዚህኑ ትእዛዞች ለልጆችህ አስተምራቸው፤ በቤት ስትቀመጥም ሆነ በመንገድ ስትሄድ፥ ዕረፍት በምታደርግበትም ጊዜ ሆነ ሥራ በምትሠራበት ጊዜ ሁሉ፥ እነዚህን ትእዛዞች ዘወትር አሰላስል፤ 8ምልክት ይሆኑህ ዘንድ በእጅህ ላይ እሰራቸው፤ በግንባርህም እንደ መለያ ለጥፋቸው። 9በቤትህ ደጃፍ መቃኖችና በቅጽር በሮችህ ላይ ጻፋቸው። #ዘዳ. 11፥18-20።
ስላለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
10“እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በገባላቸው የተሰፋ ቃል መሠረት አንተ ያልገነባሃቸው ታላላቅና የሚያማምሩ ከተሞች ያሉበትን ምድር ይሰጥሃል። #ዘፍ. 12፥7፤ 26፥3፤ 28፥13። 11የምትወርሳቸው ቤቶች አንተ ባላኖርከው መልካም ነገር የተሞሉ ይሆናሉ፤ ያልቈፈርካቸውም የውሃ ጒድጓዶች በዚያ ይገኛሉ፤ እንዲሁም አንተ ያልተከልካቸው የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ይገኛሉ፤ እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር አስገብቶህ በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ፥ 12ባሪያ ሆነህ ትኖርባት ከነበረችው ከግብጽ ምድር ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ጥንቃቄ አድርግ። 13አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት አክብረው፤ እርሱን ብቻ አምልክ፤ መሐላህም በእርሱ ስም ብቻ ይሁን። #ማቴ. 4፥10፤ ሉቃ. 4፥8። 14በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ የሚሰግዱላቸውን ሌሎችን ባዕዳን አማልክት አታምልኩ፤ 15ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ በመካከላችሁ የሚገኘውን የአምላካችሁን ቊጣ ታስነሣላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ያጠፋችኋል፤
16“ ‘ማሳህ’ ተብሎ በሚጠራው ቦታ እንዳደረጋችሁት ዐይነት እግዚአብሔር አምላካችሁን አትፈታተኑ፤ #ዘኍ. 17፥1-7፤ ማቴ. 4፥7፤ ሉቃ. 4፥12። 17እርሱ ያዘዛችሁንም ትእዛዞች፥ ድንጋጌዎችና ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ። 18በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክልና መልካም የሆነውን ሁሉ አድርግ፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንልሃል፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ በገባውም ተስፋ ቃል መሠረት መልካሚቱን ምድር ትወርሳለህ፤ 19ይህንንም የምታደርገው ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ጠላቶችህን ሁሉ በማባረር ነው።
20“በሚመጡት ዘመናት ልጅህ የእነዚህ ሕግጋት፥ ደንቦችና ሥርዓቶች ትርጒም ምንድን ነው ብሎ ሲጠይቅህ 21በዚያን ጊዜ አንተ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘ቀድሞ እኛ ለግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔር ግን በታላቅ ኀይሉ አወጣን፤ 22ግብጻውያንን፥ ንጉሣቸውንና መኰንኖቻቸውን በብርቱ የሚጐዱ ታላላቅ ተአምራትን ማድረጉን በገዛ ዐይኖቻችን ዐይተናል፤ 23ያወርሳቸው ዘንድ ለቀድሞ አባቶቻችን በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ወደዚህ አምጥቶ ይህችን ምድር ሊሰጠን ከግብጽ ነጻ አወጣን። 24ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር አምላካችን እነዚህን ደንቦች እንድንፈጽምና እርሱንም እንድንፈራው አዞናል፤ እኛም ይህን ብናደርግ እርሱ ዘወትር ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ እንዲከናወንልን ያደርጋል፤ ዛሬ እንደሚያደርገውም ሁሉ በሕይወት ያኖረናል፤ 25እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን የእርሱን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብንፈጽም ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።’

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in