YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 42

42
የእግዚአብሔር አገልጋይ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እኔ የምደግፈው የመረጥኩትና
በእርሱም ደስ የሚለኝ አገልጋዬ ይህ ነው፤
መንፈሴ በእርሱ እንዲያድርበት አደርጋለሁ፤
እርሱ ለሕዝቦች ሁሉ ትክክለኛ ፍርድን ያመጣል። #ማቴ. 3፥17፤ 17፥5፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 3፥22፤ 9፥35።
2ጮኾ አይናገርም፤
ድምጡንም በየአደባባዩ እንዲሰማ አያደርግም።
3የተቀጠቀጠ ሸምበቆን እንኳ አይሰብርም፤
ሊጠፋ የተቃረበውንም መብራት አያጠፋም፤
በታማኝነት ፍትሕን ያስገኛል።
4በምድር ላይ ፍትሕን እስኪመሠርት ድረስ
እርሱ አይታክትም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤
በሩቅ ያሉ ሕዝቦችም የእርሱን ትምህርት ለመስማት ይናፍቃሉ።” #ማቴ. 12፥18-21።
5ሰማይን የፈጠረና ከዳር እስከ ዳር የዘረጋው፥
ምድርንና በውስጥዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሠራ፥
ሕይወትንና እስትንፋስንም የሰጣቸው፥
እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ #ሐ.ሥ. 17፥24-25።
6“እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤
እጅህን ይዤ ጠብቄሃለሁ፤
ለወገኖቼ እንደ ቃል ኪዳን፥
ለአሕዛብ እንደ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ።
7ስለዚህ የዕውሮችን ዐይን ታበራለህ፤
በጨለማው ጒድጓድ እስር ቤት ውስጥ ያሉትን እስረኞችን ታወጣለህ።
8“ስሜ እግዚአብሔር ነው፤
የእኔንም ክብር የሚጋራ ሌላ አምላክ የለም፤
ጣዖቶችም ምስጋናዬን እንዲካፈሉ አልፈቅድም።
9እነሆ፥ እኔ አስቀድሜ የተናገርኳቸው ነገሮች ሁሉ ተፈጽመዋል፤
አሁን ደግሞ ወደ ፊት ስለሚሆኑት አዳዲስ ነገሮች፥
ከመፈጸማቸው በፊት እናገራለሁ።”
የምስጋና መዝሙር
10ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ!
የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ!
በባሕሩ ውስጥ ያሉት ሁሉ፥
የጠረፍ አገሮችና በእነርሱም የሚኖሩ ሁሉ ያመስግኑ!
11በረሓና በበረሓ የሚገኙ ከተሞች፦
እንዲሁም የቄዳር ሕዝቦች የሚኖሩባት መንደር ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤
የሴላዕ ከተማ ነዋሪዎች በደስታ ይዘምሩ፤
ከተራሮችም ጫፍ የእልልታ ድምፅ ያሰሙ።
12እነርሱም እግዚአብሔርን ያክብሩ፤
በጠረፍ አገሮችም ላይ ምስጋናውን ያውጁ።
13እግዚአብሔር እንደ ጀግና ወታደር ይወጣል፤
ድምፁንም ከፍ አድርጎ ጦርነትን ያውጃል፤
በጠላቶቹም ላይ ድልን ይጐናጸፋል።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመርዳት የሰጠው ተስፋ
14“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለረጅም ጊዜ ታገሥኩ፤
ጸጥ ብዬም ራሴን ገታሁ፤
አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት ከፍተኛ ድምፅ አሰማለሁ፤
የቊጣ እስትንፋስ እተነፍሳለሁ።
15ተራራዎችንና ኰረብቶችን አጠፋለሁ፤
በእነርሱ ላይ የበቀሉትን ሁሉ አደርቃለሁ፤
ወንዞችን ወደ ደረቅ ምድር እለውጣለሁ፤
ኩሬዎችንም አደርቃለሁ።
16“ዕውሮችን ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤
ቀድሞ ባላወቁትም መንገድ እመራቸዋለሁ፤
በፊታቸው የተጋረደውንም ጨለማ ወደ ብርሃንነት እለውጣለሁ፤
ወጣገባ የሆነውንም ስፍራ አስተካክላለሁ፤
እነዚህ ነገሮች ሁሉ እኔ የምፈጽማቸው ናቸው፤
አልተዋቸውምም።
17በጣዖቶች ተማምነው
ምስሎችን ‘እናንተ አምላኮቻችን ናችሁ’ የሚሉ
ኀፍረት ይደርስባቸዋል።”
እስራኤል ለመማር እምቢተኛ ስለ መሆኑ
18“እናንተ ደንቆሮዎች አድምጡ!
እናንተም ዕውሮች አተኲራችሁ ተመልከቱ!
19ከአገልጋዬ በቀር ዕውር ማነው?
ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ ማነው?
ራሱን ለእኔ እንዳስገዛው ያለው ዕውር ማን ነው?
ወይም እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ ያለ ዕውር ማን ነው?
20እስራኤል ሆይ! ብዙ ነገር አይተሃል፤
ነገር ግን ልብ ብለህ አላስተዋልከውም፤
ጆሮዎችህም ክፍት ናቸው፤ ነገር ግን አንተ አትሰማም።”
21እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርዱን ለማጠናከር
ሕጉን ታላቅና የተከበረ ያደርገው ዘንድ ፈቀደ።
22ሕዝቡ ግን ተዘርፈውና ተበዝብዘው በዋሻ ውስጥ ተዘግቶባቸዋል፤
በወህኒ ቤትም ተሸሽገዋል።
ተዘረፉ፤ ተበዘበዙ፤
ማንም በመታደግ ሊያድናቸው አልቻለም።
23ከእናንተ መካከል ለዚህ ትኲረት ሰጥቶ
ስለሚመጣው ጊዜ በጥንቃቄ የሚያዳምጥ ማነው?
24የያዕቆብን ልጆች እስራኤላውያንን ለዘራፊና ለቀማኛ አሳልፎ የሰጠ ማነው?
ይህን ያደረገው እግዚአብሔር ራሱ አይደለምን?
ይህም የሆነው እኛ ስለ በደልነው፥
በሚፈቅደው መንገድ ስላልሄድንና
ለሕጉም ታዛዦች ስላልሆንን ነው።
25ስለዚህ የቊጣውን ግለትና አስፈሪውን ጦርነት በላያችን ላይ አወረደ፤
በዙሪያችን እሳት አቀጣጠለ፤
እኛ ግን ይህን ሁሉ አልተረዳነውም፤
አቃጠለን ልብም አላደረግነውም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in