የያዕቆብ መልእክት 1
1
1በዓለም ሁሉ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው ከያዕቆብ የተላከ መልእክት፦ #ማቴ. 13፥55፤ ማር. 6፥3፤ ሐ.ሥ. 15፥13፤ ገላ. 1፥19።
ሰላም ለእናንተ ይሁን።
እምነትና ጥበብ
2ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን እንዳገኛችሁ አድርጋችሁ ቊጠሩ። 3የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥት የሚያስገኝላችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ። 4በትዕግሥት መጽናታችሁ ምንም ሳይጐድልባችሁ ፍጹምና ሙሉ እንድትሆኑ የሚያበቃችሁ ይሁን። 5ከእናንተ መካከል ጥበብ የጐደለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን ይለምን፤ እግዚአብሔርም ይሰጠዋል፤ እርሱ ምንም ቅር ሳይለው ለሁሉም በልግሥና የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው። 6ነገር ግን ሰው ምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተናወጠ የባሕር ማዕበል ይመስላል። 7እንዲህ ዐይነቱ ሰው ከጌታ ምንም ነገር የሚያገኝ አይምሰለው። 8ይህም የሚሆነው ሁለት ሐሳብ ስላለውና በመንገዱም ስለሚያወላውል ነው።
የድኻ ሰውና የሀብታም ሰው ደስታ
9በኑሮው ዝቅተኛ የሆነ ወንድም እግዚአብሔር ከፍ ስለሚያደርገው ደስ ይበለው። 10የሰው ሀብት እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በኑሮው ከፍ ያለ ወንድም እግዚአብሔር በኑሮው ዝቅ ቢያደርገውም ደስ ይበለው፤ 11ፀሐይ ከሙቀቱ ጋር ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል አበባውም ይረግፋል፤ ውበቱም ይጠፋል፤ እንዲሁም ሀብታም ሰው በሥራው ሲባክን ይጠፋል። #ኢሳ. 40፥6-7።
በሰው ላይ ስለሚደርስ ፈተና
12ጌታ በቃል ኪዳኑ መሠረት ለወዳጆቹ የሚሰጠውን የሕይወት አክሊል ስለሚቀበል ፈተናን ታግሦ የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። 13እግዚአብሔር በክፉ ነገር ስለማይፈተንና እንዲሁም እርሱ ማንንም ስለማይፈትን ሰው በሚፈተንበት ጊዜ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል። 14ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በገዛ ራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። 15ከዚህ በኋላ ምኞት ስትፀንስ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ስታድግ ሞትን ትወልዳለች።
16የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ! 17መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከብርሃን አባት ከእግዚአብሔር ነው። 18እግዚአብሔር የፍጥረቱ ሁሉ መጀመሪያ እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን።
የሰሙትን በሥራ ላይ ማዋል
19የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርና ለቊጣም የዘገየ ይሁን። 20የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያስገኝም። 21ስለዚህ ርኲሰትንና የክፋትንም ብዛት ሁሉ አስወግዳችሁ እግዚአብሔር በልባችሁ የተከለውንና ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ።
22ቃሉን በሥራ ላይ የምታውሉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ። 23ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ሰው የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ 24ይህ ሰው ፊቱን በመስተዋት ካየ በኋላ ይሄዳል፤ እንዴት እንደ ሆነም ወዲያውኑ ይረሳዋል። 25ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ መርምሮ በእርሱ የሚጸና፥ እርሱንም ሰምቶ መርሳት ሳይሆን፥ በሥራ ላይ የሚያውለው ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል።
26አንደበቱን ሳይቈጣጠር እግዚአብሔርን አመልካለሁ የሚል ሰው ራሱን ያታልላል፤ የእርሱም አምልኮ ከንቱ ነው። 27በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ ሃይማኖት “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።”
Currently Selected:
የያዕቆብ መልእክት 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997