ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3
3
እውነተኛ ጽድቅ
1በመጨረሻም ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ያንን ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁን ነገር ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔን አያሰለቸኝም፤ እናንተን ግን ከስሕተት ሊጠብቃችሁ ይችላል። 2እንደ ውሻ ከሚልከፈከፉ ከክፉ አድራጊዎች ተጠንቀቁ፤ ሥጋን ከሚቈራርጡ (ከሚገርዙ) ተጠንቀቁ። 3እኛ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናመልክና በውጭ በሚታየው ሥርዓት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የምንመካ ስለ ሆንን በእውነት ተገርዘናል። 4ትምክሕት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ በብዙ ነገር ልመካ እችላለሁ፤ በውጭ በሚታየው ሥርዓት የሚመካ ሰው ቢኖር እኔ ከእርሱ ይበልጥ የምመካበት ብዙ ምክንያት አለኝ። 5እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዤአለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ነገድ የሆንኩ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም የተነሣ ጥርት ያልኩ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁድን ሕግ ስለ መጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበር። #ሐ.ሥ. 23፥6፤ 26፥5፤ ሮም 11፥1። 6ስለ ኦሪት ሕግ በመቅናትም ቢሆን የቤተ ክርስቲያንን አማኞች አሳድ ነበር። ሕግን በመጠበቅ ስለ መጽደቅም ቢሆን ያለ ነቀፋ እኖር ነበርኩ። #ሐ.ሥ. 8፥3፤ 22፥4፤ 26፥9-11። 7እንግዲህ ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው ከንቱ ነገሮች አድርጌ እቈጥራቸዋለሁ። 8ከዚህም በቀር ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቅ የበለጠ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ ስለማምን ሁሉን ነገር እንደ ኪሣራ እቈጥረዋለሁ፤ ስለ እርሱም ሁሉን ነገር አጥቻለሁ። ክርስቶስንም ለማግኘት ስል ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቈጥራለሁ። 9ይህንንም የማደርግበት ምክንያት በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴን ጽድቅ ትቼ በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በክርስቶስ በማመን ለማግኘትና ከእርሱም ጋር ለመሆን ነው። 10ሌላው ምክንያት ክርስቶስንና የክርስቶስን የትንሣኤ ኀይል ለማወቅ፥ የመከራው ተካፋይ ለመሆንና በሞቱም እርሱን ለመምሰል ነው። 11እንዲሁም ከሞትኩ በኋላ ተነሥቼ ለዘለዓለም በሕይወት ለመኖር ተስፋ በማድረግ ነው።
ወደ ግብ ለመድረስ መሮጥ
12ይህን ሁሉ ገና አላገኘሁም፤ ወይም በዚህ ሁሉ ፍጹም ሆኜአለሁ ለማለት አልችልም፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔን የእርሱ አድርጎ ያዘጋጀልኝን ሽልማት ለማግኘት ወደፊት በመሮጥ እተጋለሁ። 13ወንድሞቼ ሆይ! ገና ወደዚያ እንደ ደረስኩ አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ይኸውም በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። 14ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው።
15እንግዲህ በመንፈሳዊ ሕይወት የጠነከርን ሁሉ ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፤ የምትለያዩበት ሐሳብ በመካከላችሁ ቢኖር ይህንንም ሐሳብ እግዚአብሔር ግልጥ ያደርግላችኋል። 16ያም ሆነ ይህ እስከ አሁን ከደረስንበት መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ይሁን።
17ወንድሞች ሆይ! የእኔን ምሳሌነት ለመከተል ተባበሩ፤ የእኛንም ምሳሌነት የሚከተሉትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። #1ቆሮ. 4፥16፤ 11፥1። 18ከአሁን በፊት ብዙ ጊዜ እንደ ነገርኳችሁና አሁንም እንባዬን እያፈሰስኩ እንደምነግራችሁ ሁሉ ብዙዎቹ በአካሄዳቸው የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነዋል። 19የእነርሱ አምላክ ሆዳቸው ነው፤ አሳፋሪ የሆነ ነገር ለእነርሱ ክብራቸው ነው፤ ሐሳባቸውም የሚያተኲረው በምድራዊ ነገር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእነርሱ መጨረሻ ጥፋት ነው። 20እኛ ግን የሰማይ መንግሥት ዜጎች ነን፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን። 21እርሱ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ የእርሱን ክቡር ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል፤ ይህንንም የሚያደርገው ሁሉን በሥልጣኑ ሥር ለማድረግ በሚያስችለው ኀይል ነው።
Currently Selected:
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997