YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 14

14
1ጥበበኛ ሴት ቤትዋን በሥነ ሥርዓት ታስተዳድራለች፤
ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጅዋ ታፈርሰዋለች።
2አካሄዱ ቀጥተኛ የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤
መንገዱ ጠማማ የሆነ ሰው ግን እግዚአብሔርን አይፈራም።
3ሞኝን የገዛ ንግግሩ ያስቀጣዋል፤
ጥበበኞችን ግን መልካም አነጋገራቸው ይጠብቃቸዋል።
4የምታርስባቸው በሬዎች ከሌሉህ ጐተራህ ባዶ ይሆናል።
በሬዎች ካሉህ ግን ጐተራህ በእህል የተሞላ ይሆናል።
5ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤
ሐሰተኛ ምስክር ግን የሚናገረው ሐሰት ነው።
6ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል፤ አያገኛትም።
አስተዋዮች ግን ዕውቀትን በቀላሉ ይገበያሉ።
7ከእነርሱ የምትማረው ምንም ዕውቀት ስለሌለ ከሞኞች ራቅ።
8የብልኅ ሰው ጥበብ መንገዱን እንዳይስት ያደርገዋል።
ሞኝን ሰው ግን ሞኝነቱ መንገዱን እንዲስት ያደርገዋል።
9ሞኞች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤
ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ።
10ደስታህም ሆነ ሐዘንህ የራስህ ነው፤
ማንም የሚካፈልህ የለም።
11የክፉ ሰው ቤት ይፈርሳል፤
የደግ ሰው ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።
12አንተ “ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለህ
የምታስበው ወደ ሞት ይመራህ ይሆናል። #ምሳ. 16፥25።
13በሳቅ ጊዜ እንኳ በልብ ውስጥ ሐዘን ሊኖር ይችላል፤
የደስታም ፍጻሜ ለቅሶ ነው።
14ከሐዲዎች ሰዎች የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤
ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።
15ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤
ብልኆች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ።
16ብልኆች እግዚአብሔርን ስለሚፈሩ ከክፉ ነገር ለመራቅ ይጠነቀቃሉ፤
ሞኞች ግን ከአደጋ የማይጠነቀቁ ችኲሎች ናቸው።
17ቊጡ ሰው የሞኝነትን ሥራ ይሠራል፤
ጥበበኛ ግን ይታገሣል።
18አላዋቂዎች የስንፍናቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤
ብልኆች ግን ዕውቀትን እንደ አክሊል ይቀዳጃሉ።
19ክፉዎች በደጋግ ሰዎች ፊት ይንበረከካሉ፤
ኃጢአተኞች በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ።
20ድኻ ሰው በጐረቤቱ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው።
ሀብታሞች ግን ብዙ ወዳጆች አሉአቸው።
21ሰዎችን የሚንቅ ኃጢአተኛ ነው፤
ለድኾች የሚራራ ግን የተባረከ ነው፤
22ክፉ የሚያቅዱ ሰዎች ስሕተተኞች አይደሉምን?
መልካምን ነገር የሚያቅዱ ግን ምሕረትንና ታማኝነትን ያገኛሉ።
23ተግቶ መሥራት ጥቅምን ያስገኛል፤
ወሬኛነት ግን ያደኸያል።
24የብልኆች ዘውድ ጥበባቸው ነው፤
የሞኞች ጌጥ ግን ሞኝነታቸው ነው።
25እውነትን የሚናገር ምስክር ሕይወትን ያድናል፤
ሐሰት የሚናገር ምስክር ግን አታላይ ነው።
26እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው
ለራሱና ለቤተሰቡ ጽኑ መታመኛና ዋስትና አለው።
27እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤
ስለዚህ ከሞት ወጥመድ ለማምለጥ ከፈለግህ እግዚአብሔርን ፍራ።
28የንጉሥ ታላቅነት የሚለካው በሚያስተዳድራቸው ሕዝብ ብዛት ነው፤
የሚገዛው ሕዝብ ከሌለው ግን ለንጉሡ ጥፋት ነው።
29ትዕግሥተኛ ብትሆን አስተዋይ መሆንህን ትገልጣለህ፤
ቊጡ ብትሆን ግን ስንፍናህን ታሳያለህ።
30ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል፤
ቅንአት ግን አጥንትን ያደቃል።
31ድኾችን ማስጨነቅ ፈጣሪን መናቅ ነው፤
ለድኾች ቸርነትን ማድረግ ግን
እግዚአብሔርን እንደ ማክበር ይቈጠራል።
32ችግር ሲመጣ ክፉዎች ይወድቃሉ፤
ጻድቃን ግን በታማኝነታቸው ይጠበቃሉ።
33የአስተዋይ ሰው ልብ ጥበብን የተሞላ ነው፤
በሞኞች ልብ ግን ጥበብ አትታወቅም።
34እውነተኛነት አንድን ሕዝብ ታላቅ ያደርገዋል፤
ኃጢአት ግን ማንኛውንም ሕዝብ ያዋርዳል።
35ነገሥታት ችሎታ ባላቸው አገልጋዮች ይደሰታሉ፤
አሳፋሪ አገልጋዮች ግን ንጉሡን ያስቈጣሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in