YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 27

27
(የዳዊት መዝሙር)
የምስጋና ጸሎት
1እግዚአብሔር ብርሃኔና ደኅንነቴ ስለ ሆነ ማንንም አልፈራም
እግዚአብሔር የሕይወቴ ከለላ ስለ ሆነ የሚያስፈራኝ ማነው?
2ክፉ ሰዎች ሲያጠቁኝና ሊገድሉኝ ሲቃጡ
እነርሱ ራሳቸው ተሰናክለው ይወድቃሉ።
3ብዙ ሠራዊት ቢከበኝም አልፈራም፤
ጠላቶቼ በጦርነት ቢያጠቁኝ እንኳ
በእግዚአብሔር መተማመኔን አልተውም።
4እግዚአብሔርን አንድ ነገር እለምነዋለሁ፤
የምለምነውም፦
በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ
የእግዚአብሔርን አስደናቂነት እንድመለከትና
በቤተ መቅደሱም መጸለይ እንድችል ነው።
5በችግር ቀን በጥላው ሥር ይደብቀኛል፤
በመቅደሱ ውስጥ ይሰውረኛል፤
በአለትም ላይ ከፍ አድርጎ ይጠብቀኛል።
6አሁን ግን በከበቡኝ ጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ አደረግሁ፤
በደስታ “እልል” እያልኩ
በመቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት አቀርባለሁ፤
እየዘመርኩም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
7እግዚአብሔር ሆይ!
ወደ አንተ ጮክ ብዬ ስጣራ ስማኝ!
ምሕረትን አድርግልኝ፤ ጸሎቴንም ስማ!
8ልቤ “የእርሱን ፊት ፈልግ” አለኝ፤
እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን ፊት እሻለሁ።
9አምላኬና አዳኜ ሆይ!
ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ፤
ተቈጥተህም እኔን አገልጋይህን ከአንተ እንድርቅ አታድርገኝ፤
ረዳቴም ስለ ሆንክ ከእኔ አትለይ፤ አትተወኝም።
10አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ
እግዚአብሔር ዘወትር ይቀበለኛል።
11እግዚአብሔር ሆይ! የምመራበትን መንገድ አስተምረኝ፤
በጠላቶቼም ምክንያት በተደላደለ መንገድ ምራኝ።
12የሐሰት ምስክሮች ዐመፅን እየተናገሩ በእኔ ላይ ስለ ተነሡ
ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ።
13ሕያዋን በሚኖሩባት ምድር እስካለሁ ድረስ
የእግዚአብሔርን በጎነት እንደማይ እተማመናለሁ።
14በእግዚአብሔር ታመን፤
በርታ፤ ተስፋ አትቊረጥ፤
በእግዚአብሔር ታመን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in