YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 31

31
በእግዚአብሔር የመታመን ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ!
መጠጊያ እንድትሆነኝ ወደ አንተ መጥቻለሁ፤
ስለዚህ እንዳፍር አታድርገኝ፤
በጽድቅህም አድነኝ።
2ጌታ ሆይ! አድምጠኝ፤
ፈጥነህም በመምጣት አድነኝ፤
መጠጊያ አለትና ጠንካራ ምሽግ ሆነህ አድነኝ።
3አንተ መጠጊያ ምሽጌ ነህ፤
ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤
የምሄድበትንም መንገድ አሳየኝ።
4አንተ መጠጊያዬ ስለ ሆንክ
ጠላቶቼ ከዘረጉብኝ ወጥመድ አውጣኝ።
5የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ!
ነፍሴን ለአንተ እሰጣለሁና አድነኝ። #ሉቃ. 23፥46።
6ዋጋቢሶች ለሆኑ ጣዖቶች
የሚሰግዱትን ሁሉ ትጠላለህ፤
እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ።
7ስለ ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ደስ ይለኛል፤
ሐሴትም አደርጋለሁ፤
መከራዬን አይተህ ጭንቀቴን ታውቃለህ፤
8ለጠላቶች አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤
ነገር ግን ሰፊ መንገድ ከፈትክልኝ።
9እግዚአብሔር ሆይ! በችግር ላይ ስለ ሆንኩ
ምሕረትን አድርግልኝ፤
ዐይኖቼ፥ ነፍሴና ሥጋዬ በሐዘን ደክመዋል።
10ሕይወቴ በሐዘን ዕድሜዬም በመቃተት አለቀ፤
በችግሬ ምክንያት ኀይል አጣሁ፤
አጥንቶቼም ደከሙ።
11እኔ የጠላቶቼ መሳለቂያ፥
ለጐረቤቶቼ አስደንጋጭ፥
ለሚያውቁኝም አስፈሪ ነኝ፤
በመንገድ ሲያዩኝም ከእኔ ይሸሻሉ።
12እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤
ተሰብሮ እንደ ተጣለ የሸክላ ዕቃ ሆንኩ።
13የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁ፤
በሁሉም አቅጣጫ ፍርሀት አለ፤
በእኔ ላይ ያሤራሉ፤
ሊገድሉኝ በማቀድ ያድማሉ።
14እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤
እኔ በአንተ እታመናለሁ።
15እኔ ሁልጊዜ በአንተ እጅ ነኝ፤
ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ።
16ወደ አገልጋይህ በፈገግታ ተመልከት፤
በዘለዓለማዊ ፍቅርህም አድነኝ።
17እግዚአብሔር ሆይ!
ወደ አንተ በምጣራበት ጊዜ አታሳፍረኝ፤
ክፉዎች ግን ይፈሩ፤
ጸጥ ብለውም ወደ ሲኦል ይውረዱ።
18በጻድቅ ላይ በትዕቢትና በንቀት
በኩራትም ስለሚናገር
የሐሰት አንደበታቸውን ጸጥ አሰኝ።
19በአንተ ለመከለል ወደ አንተ ለሚጠጉ
በሰዎች ሁሉ ፊት የምትሰጠው
ለሚፈሩህ ያዘጋጀኸው ደግነት
ምንኛ ትልቅ ነው!
20ከሚያሤሩባቸው ሰዎች በመኖሪያህ ጥላ ሥር ትደብቃቸዋለህ፤
ከመርዘኛ አንደበትም በከለላህ ትጠብቃቸዋለህ።
21በተከበበች ከተማ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ
በሚያስደንቅ ሁኔታ ዘላቂ ፍቅሩን
የገለጠልኝ እግዚአብሔር ይመስገን!
22ከድንጋጤዬ የተነሣ
ከፊትህ ያራቅኸኝ መስሎኝ ነበር፤
ነገር ግን ርዳታህን ፈልጌ ለምሕረት ወደ አንተ ስጣራ
ጩኸቴን ሰማህ።
23እናንተ ለእርሱ የተቀደሳችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን ውደዱት፤
እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤
ለትዕቢተኞች ግን ተገቢ ቅጣታቸውን ይሰጣል።
24እናንተ በእግዚአብሔር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ
ጠንክሩ፤ በርቱም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in