የዮሐንስ ራእይ 2
2
(1) የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን
1ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
“ይህ ሰባቱን ኮከቦች በቀኝ እጁ ከያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል ከሚመላለሰው የተነገረ ነው፤ 2ሥራህን፥ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ክፉዎችን ግን ልትታገሣቸው እንዳልቻልክ፥ ሐዋርያት ሳይሆኑም ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ። 3በትዕግሥት መጽናትህንና ስለ ስሜም ሳትሰለች መከራ መቀበልህን ዐውቃለሁ፤ 4ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል፤ 5ከምን ያኽል ከፍተኛ ቦታ ላይ መውደቅህን አስታውስ! ንስሓም ግባ! በመጀመሪያ ታደርገው የነበረውን ሥራህን አድርግ፤ ይህን ሁሉ ባታደርግ ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ንስሓም ካልገባህ መቅረዝህን ከስፍራው አነሣዋለሁ። 6ነገር ግን የሚያስመሰግንህ አንድ ነገር አለ፤ ይህም እኔ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃል።
7“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! ‘ድል ለሚነሣ በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ካለው ከሕይወት ዛፍ ፍሬ እንዲበላ አደርገዋለሁ።’ #ዘፍ. 2፥9፤ ራዕ. 22፥2፤ ሕዝ. 28፥13፤ 31፥8።
(2) የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን
8“ለሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ #ኢሳ. 44፥6፤ 48፥12፤ ራዕ. 1፥17፤ 22፥13።
“ይህ፥ የመጀመሪያና የመጨረሻ ከሆነው፥ ሞቶ ከነበረውና ሕያው ከሆነው የተነገረ ነው፤ 9መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ፥ የሰይጣን ማኅበር የሆኑ፥ ስምህን እንዳጠፉት ዐውቃለሁ፤ 10ወደ ፊት የሚደርስብህን መከራ አትፍራ፤ እነሆ፥ እንድትፈተኑ ከእናንተ አንዳንዶቹን ዲያብሎስ ወደ እስር ቤት ያገባችኋል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ፤ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ የሕይወት አክሊል እሰጥሃለሁ።
11“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!
“ድል የሚነሣ በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።” #ራዕ. 20፥14፤ 21፥8።
(3) የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን
12“ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
“ይህ፥ በሁለት በኩል ስለት ያለውን ሰይፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ 13አንተ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ስፍራ መኖርህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል፤ በእኔ ላይ ያለህን እምነት አልካድክም፤ ታማኝ ምስክሬ የነበረው አንቲጳስ ሰይጣን በሚኖርበት በእናንተ ከተማ በተገደለ ጊዜ እንኳ በእኔ ማመንህን አልተውክም። 14ነገር ግን የምነቅፍብህ አንዳንድ ነገሮች አሉኝ፤ ይኸውም የበለዓምን ትምህርት የያዙ አንዳንድ ሰዎች በመካከላችሁ አሉ፤ ይህ በለዓም የእስራኤል ሕዝብ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ በመብላትና ዝሙት በማድረግ እንዲሰናከሉ ባላቅን የመከረ ነው። #ዘኍ. 22፥5፤7፤ 31፥16፤ ዘዳ. 23፥4፤ ዘኍ. 25፥1-3። 15እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት የያዙ ሰዎችም በመካከላችሁ አሉ፤ 16ስለዚህ ንስሓ ግባ፤ አለበለዚያ በቶሎ ወደ አንተ መጥቼ እንደ ሰይፍ ባለው ከአፌ በሚወጣው ቃል እዋጋቸዋለሁ።
17“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይም እሰጠዋለሁ፤ ከተቀባዩ በቀር ይህን ሌላ ማንም አያውቀውም። #ዘፀ. 16፥14-15፤ 16፥33-34፤ ዮሐ. 6፥48-50፤ ኢሳ. 62፥2፤ 65፥15።
(4) የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን
18“ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
“ይህ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ዐይኖች ካሉትና በእሳት ፍም የነጠረ ናስ የሚመስሉ እግሮች ካሉት፥ ከእግዚአብሔር ልጅ የተነገረ ነው፤ 19ሥራህንና ፍቅርህን፥ እምነትህንና አገልግሎትህን፥ በትዕግሥት መጽናትህንም ዐውቃለሁ፤ የኋለኛው ሥራህ ከፊተኛው እንደሚበልጥም ዐውቃለሁ። 20ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም ‘ነቢይት ነኝ’ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለህ ታግሠሃታል፤ እርስዋ አገልጋዮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በማስተማር አሳስታቸዋለች። #1ነገ. 16፥31፤ 2ነገ. 9፥22፤30። 21ንስሓ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ እርስዋ ግን ከዝሙትዋ ንስሓ መግባትን አልፈለገችም። 22ስለዚህ በሥቃይ አልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርስዋ ጋር ከሠሩት ከክፉ ሥራቸው ንስሓ ገብተው ካልተመለሱ በቀር ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩትንም ሁሉ ብርቱ ሥቃይ አመጣባቸዋለሁ፤ 23ልጆችዋንም በሞት እቀጣለሁ፤ አብያተ ክርስቲያንም ሁሉ የሰውን ሐሳብና ምኞት የምመረምር እኔ መሆኔን ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደየሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።
24“በትያጥሮን ላላችሁትና ይህን መጥፎ ትምህርት ላልተቀበላችሁት ሁሉ፥ እንዲሁም አንዳንዶች ‘የሰይጣን ጥልቅ ምሥጢር ነው’ የሚሉትን ላልተከተላችሁ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤ 25ሆኖም እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። 26ድል ለሚነሣ፥ በሥራዬም ላይ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ 27‘በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ቀጥቅጦ ያደቃቸዋል፤’ ይህም ሥልጣን እኔ ከአባቴ እንደ ተቀበልኩት ዐይነት ነው፤ 28የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ።
29“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 2: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997