መጽሐፈ ሩት 2
2
ሩት በቦዔዝ እርሻ ልትቃርም መሰማራትዋ
1ለናዖሚም ሀብታምና ታዋቂ የሆነ ቦዔዝ የሚባል የባልዋ የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ 2አንድ ቀን ሞአባዊትዋ ሩት ናዖሚን “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው እርሻ ሄጄ ቃርሚያ ልቃርም” አለቻት። ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሂጂ!” አለቻት። #ዘሌ. 19፥9-10፤ ዘዳ. 24፥19።
3ሩትም ወደ እርሻዎች ሄደች፤ ከአጫጆች ኋላ እየተከተለችም ከእጃቸው የወዳደቀውን ዛላ ትቃርም ጀመር፤ እንደ አጋጣሚ የምትቃርምበት ቦታ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነው የቦዔዝ እርሻ ነበር። 4ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦዔዝ ራሱ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ እርሻው መጣ፤ አጫጆቹንም “እንደምን ዋላችሁ! እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” አላቸው።
እነርሱም “እግዚአብሔር አንተንም ይባርክህ!” አሉት።
5ከዚህ በኋላ ቦዔዝ የአጫጆቹ ኀላፊ የሆነውን ሰው “ያቺ ወጣት ሴት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው።
6ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እርስዋ ናዖሚን ተከትላ ከሞአብ አገር የመጣች ሞአባዊት ናት፤ 7አጫጆችን ተከትላ ከነዶ መካከል የወዳደቀውን ዛላ ለመቃረም እንድፈቅድላት ጠየቀችኝ፤ ከጧት ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ነበር፤ አሁን ግን ትንሽ ዕረፍት ለማድረግ ወደ ዳስ ተጠግታለች።”
8በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ! ስሚ እዚህ ያሉትን ሴቶች ሠራተኞችን ተከትለሽ ቃርሚ እንጂ ይህን እርሻ ትተሽ ለመቃረም ወደ ሌላ ቦታ አትሂጂ። 9እነርሱ የት እንደሚያጭዱ በመጠባበቅ እየተመለከትሽ ከእነርሱ ጋር ሁኚ፤ ወንዶች ሠራተኞቼን እንዳያስቸግሩሽ አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃም በሚጠማሽ ጊዜ እነርሱ ሞልተው ወዳስቀመጡአቸው እንስራዎች እየሄድሽ ቀድተሽ ጠጪ።”
10እርስዋም ግንባርዋ መሬት እስኪነካ ድረስ እጅ ነሥታ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ እንዴት በፊትህ ሞገስ ላገኝ ቻልኩ?” አለችው።
11ቦዔዝም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ባልሽ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን መልካም ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፥ የትውልድ አገርሽንም ትተሽ ከዚህ በፊት በማታውቂው ሕዝብ መካከል ለመኖር ወደዚህ እንደ መጣሽ ሰምቼአለሁ። 12እግዚአብሔር ላደረግሽው በጎ ነገር ዋጋሽን ይክፈልሽ! የእርሱን ጥበቃ ተማምነሽ የመጣሽው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዋጋሽን የተትረፈረፈ ያድርገው!”
13ሩትም “ጌታዬ ሆይ! ምንም እንኳ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ባልሆን እኔን አገልጋይህን በመልካም ቃላት አጽናንተኸኛል፤ ይህ በፊትህ ያገኘሁት ሞገስ እንዲቀጥል ፍቀድልኝ!” አለችው።
14በምሳ ሰዓት ቦዔዝ ሩትን “ነይ ወደ ገበታው ቅረቢ፤ በወጡም እያጠቀስሽ እንጀራ ብዪ” አላት። እርስዋም ከአጫጆቹ ጋር ተቀመጠች፤ ቦዔዝም የተጠበሰ እሸት ሰጣት፤ እስክትጠግብ ድረስ በላች፤ ምግብም ተርፏት ነበር። 15እንደገናም ልትቃርም ስትነሣ ቦዔዝ ጐልማሶቹን እንዲህ አላቸው፦ “በነዶዎች መካከል ያለውንም እንኳ ቢሆን ትቃርም፤ እናንተም አትከልክሉአት፤ 16እንዲያውም ከታሰረው ነዶ እየመዘዛችሁ ተዉላትና ትቃርም፤ አትቈጣጠሩአት።”
17ሩትም እስከ ምሽት ድረስ ከእርሻው እህል ስትቃርም ዋለች፤ ባሸችውም ጊዜ ዐሥር ኪሎ ያኽል ሆነ።
18እህሉንም ተሸክማ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ምን ያኽል እንደ ሰበሰበችም ለዐማትዋ አሳየቻት፤ ከምሳዋ ተርፎአት የነበረውንም ምግብ ሰጠቻት። 19ዐማትዋ “ዛሬ ከየት ቃረምሽ? ወደየትስ ሠራሽ? ይህን መልካም አቀባበል ያደረገልሽን ሰው እግዚአብሔር ይባርከው!” አለቻት።
ሩትም “እኔ ስቃርም የዋልኩበት እርሻ ባለቤት ቦዔዝ የሚባል ሰው ነው” ብላ ለናዖሚ ነገረቻት።
20ናዖሚም “ለሕያዋንና ለሙታን የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽም አምላክ ቦዔዝን ይባርከው!” አለች፤ ቀጥላም “ያ ሰው እኮ የቅርብ ዘመዳችን ነው! እንዲያውም ለእኛ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት ካለባቸው ሰዎች አንዱ እርሱ ነው” አለች። #ዘሌ. 25፥25።
21ደግሞም ሩት “መከሩን ሰብስበው እስከሚጨርሱ ድረስ ከአጫጆቹ ተጠግተሽ ቈዪ አለኝ” አለቻት።
22ናዖሚም “እውነት ነው ልጄ፤ በቦዔዝ እርሻ ካሉት ሴቶች ጋር ሆነሽ ብትቃርሚ ይሻልሻል፤ ወደ ሌላ ሰው እርሻ ብትሄጂ ግን ምናልባት ጐልማሶች ያስቸግሩሻል” አለቻት። 23ስለዚህ ሩት የገብሱና የስንዴው መከር ተሰብስቦ እስኪያበቃ ድረስ በቦዔዝ ገረዶች አጠገብ እየቃረመች ቈየች፤ ከዐማትዋም ሳትለይ አብራ ተቀመጠች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሩት 2: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997