YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ሩት 3

3
ሩት ባል ማግኘትዋ
1አማትዋ ናዖሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። 2ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ የቅርብ ዘመዳችን ነው፤ እነሆ! እርሱ ዛሬ ማታ ገብስ ይወቃል፤ 3ስለዚህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፤ የክት ልብስሽንም ልበሺ፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። 4የት እንደሚተኛ ካረጋገጥሽ በኋላ፥ እንቅልፍ ሲወስደው ወደ እርሱ ቀረብ በዪና ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።”
5ሩትም “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት።
6ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው ሄዳ ልክ ዐማትዋ እንደ ነገረቻት አደረገች። 7ቦዔዝ ከበላና ከጠጣ በኋላ ደስ ብሎት ነበር፤ ወደ ገብሱም ክምር ሄዶ ጋደም አለና አንቀላፋ፤ ሩትም በቀስታ ወደ እርሱ ተጠጋች፤ ልብሱንም ገለጥ አድርጋ በእግሩ አጠገብ ተኛች። 8ወደ እኩለ ሌሊት ገደማም ቦዔዝ ድንገት ነቅቶ ሲገላበጥ አንዲት ሴት በግርጌ ተኝታ በማግኘቱ ተደነቀ፤ 9“አንቺ ማን ነሽ?” ብሎም ጠየቃት።
እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! አገልጋይህ እኔ ሩት ነኝ፤ አንተ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ለእኔ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት አለብህ፤ ስለዚህ ልብስህን ባገልጋይህ ላይ ጣል አለችው።”
10ቦዔዝም እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ አሁን በምታደርጊው ነገር ከዚህ በፊት ለዐማትሽ ካደረግሽው የሚበልጥ ታማኝነት አሳይተሻል፤ ብትፈልጊ ኖሮ ወደ ሀብታም ወይም ወደ ድኻ ወጣት መሄድ ትችይ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልፈለግሽም፤ 11ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ መልካም ሴት መሆንሽን ያውቃሉ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ። 12እኔ የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ ይልቅ ቅርብ የሆነ ሌላ ዘመድ አለ፤ #ሩት 2፥20። 13እስኪነጋ እዚሁ ቈዪ! ሲነጋም ያ ሰው ስለ አንቺ ኀላፊነትን የሚወስድ መሆኑን ወይም አለመሆኑን እጠይቀዋለሁ፤ እርሱ ኀላፊነትን የሚወስድ ከሆነ መልካም ነው፤ የማይወስድ ከሆነ ግን ስለ አንቺ ኀላፊነትን እኔ እንደምወስድ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ አሁንም ተኚ፤ እስኪነጋም ድረስ እዚሁ ቈዪ።”
14ስለዚህ ሩት በቦዔዝ እግር አጠገብ ተኛች፤ ነገር ግን ቦዔዝ ወደ ዐውድማው እንደ መጣች ማንም እንዲያውቅ ስላልፈለገ ማንም ሊያያት በማይችልበት ሰዓት በማለዳ ከመኝታዋ ተነሣች። 15ቦዔዝም “ሸማሽን ከላይሽ አንሺና ወደዚህ ዘርጊው” አላት። እርስዋም ሸማዋን ዘረጋች፤ ቦዔዝም ወደ ኻያ ኪሎ የሚጠጋ ገብስ ሰፈረላትና አንሥቶ በትከሻዋ አሸከማት። ከዚያም እርሱ ወደ ከተማ ሄደ። 16ወደ ዐማትዋም በመጣች ጊዜ ዐማትዋ “ልጄ ሆይ! ያ ጉዳይ እንዴት ሆነልሽ?” አለቻት። ሩትም ቦዔዝ ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት። 17ደግሞም “ወደ ዐማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ” ብሎ ይህን ኻያ ኪሎ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።
18ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሰውዬው ይህን ነገር ዛሬ እስኪፈጽም ድረስ አያርፍምና፥ ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ጠብቂ” አለቻት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in