ወደ ቲቶ 2
2
ስለ ትክክለኛ እምነት
1አንተ ግን ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት አስተምር፤ 2በዕድሜ የገፉ ወንዶች፥ በመጠን የሚኖሩ፥ ክብራቸውን የሚጠብቁ፥ ጠንቃቆች፥ በእምነትና በፍቅር በትዕግሥትም ጤናማዎች እንዲሆኑ ምከራቸው። 3እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሴቶች በጠባያቸው የተከበሩ እንዲሆኑ እንጂ ሐሜተኞችና፥ የመጠጥ ሱሰኞች እንዳይሆኑና መልካሙን ትምህርት እንዲያስተምሩ ምከራቸው። 4እንዲሁም ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ፥ 5ጠንቃቆችና ንጹሖች፥ ደጎች፥ ለባሎቻቸውም የሚታዘዙ እንዲሆኑ ያስተምሩአቸው። ይህንንም የሚያደርጉት የእግዚአብሔር ቃል እንዳይነቀፍ ነው።
6እንዲሁም ጐልማሶች ራሳቸውን በመቈጣጠር እንዲኖሩ ምከራቸው። 7አንተም መልካም የሆነውን እያደረግህ በሁሉ ነገር ምሳሌ ሁንላቸው፤ በትምህርትም እውነተኛነትን፥ ቁምነገረኛነትን አሳይ፤ 8የማይነቀፍ ጤናማ ንግግርን ግለጥላቸው፤ በዚህ ዐይነት ተቃዋሚዎች በእኛ ላይ የሚናገሩት ክፉ ነገር ሲያጡ ያፍራሉ።
9አገልጋዮችም ለጌቶቻቸው እንዲታዘዙ፥ በሁሉም ነገር እንዲያስደስቱአቸው፥ ክፉ ቃል እንዳይመልሱላቸው፥ 10ገንዘባቸውንም እንዳይሰርቁአቸው ምከራቸው፤ ይልቅስ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት በሁሉ ነገር እንዲከበር ሁልጊዜ ፍጹም ታማኝነትን ያሳዩ።
11እግዚአብሔር ሰውን የሚያድንበትን ጸጋውን ለሁሉም ገልጦአል፤ 12ይህም ጸጋ ክሕደትንና ሥጋዊ ምኞትን በመተው ራስን በመቈጣጠር፥ በቀጥተኛነትና በመንፈሳዊነት በዚህ ዓለም እንድንኖር ያስተምረናል። 13በዚህ ዐይነት የተባረከውን ተስፋችንን እንዲሁም የታላቁ አምላካችንን፥ የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በክብር መገለጥ እንጠባበቃለን። 14ክርስቶስ ከዐመፃ ሁሉ ሊያድነንና መልካም ሥራ ለመሥራት ትጉሆችና ለእርሱ የተለየን ንጹሕ ሕዝብ እንድንሆን ያነጻን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። #መዝ. 130፥8፤ ዘፀ. 19፥5፤ ዘዳ. 4፥20፤ 7፥6፤ 14፥2፤ 1ጴጥ. 2፥9።
15እንግዲህ እነዚህን ነገሮች አስተምር፤ በሙሉ ሥልጣንም ምከር፤ ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።
Currently Selected:
ወደ ቲቶ 2: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997