1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1
1
ሰላምታና ምስጋና
1በእግዚአብሔር ጥሪና ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ጳውሎስ፥ ከወንድማችንም ሶስቴንስ፥ 2#የሐዋ. 18፥1።በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር፤
3ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
4በክርስቶስ ኢየሱስ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 5በንግግር ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በሁሉም ነገር በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና፤ 6ለክርስቶስ እንደ ምስክርነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል። 7እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ፥ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ 8እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። 9ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ የጠራችሁ፥ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
1 ክፍፍል እና ነውር
ሀ. በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረ መለያየት
በክርስቲያኖች መካከል መለያየት
10ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ሁላችሁ ተስማምታችሁ በአንድ ልቡና እና በአንድ አቋም በአንድነት የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11ወንድሞቼ ሆይ! በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ የቀሎኤ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። 12#የሐዋ. 18፥24።እኔ የምለው፥ እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤” “እኔስ የአጵሎስ ነኝ፤” “እኔ ግን የኬፋ ነኝ፤” “እኔስ የክርስቶስ ነኝ፤” ትላላችሁ። 13ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነበር? 14#የሐዋ. 18፥8፤ የሐዋ. 19፥29፤ ሮሜ 16፥23።ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 15ማንም በስሜ ተጠመቃችሁ ሊል አይገባውም። 16#1ቆሮ. 16፥15።የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ከነዚህ ሌላ አጥምቄ እንደሆነ አላውቅም። 17ወንጌልን ላስተምር እንጂ ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝም፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር፥ በቃል ጥበብም አይደለም።
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ መሆኑ
18የመስቀሉ መልዕክት ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው።
19 #
ኢሳ. 29፥14። “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤
የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ፤”
ተብሎ ተጽፎአልና። 20#ኢዮብ 12፥17፤ ኢሳ. 19፥12፤ 33፥18፤ ኢሳ. 44፥25።ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚህ ዘመን ተከራካሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? 21#ጥበ. 13፥1-9።በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በምንሰብከው ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል። 22መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፤ ግሪኮችም ጥበብን ይሻሉ፤ 23እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፤ 24ለተጠሩት ግን፥ ለአይሁዶች ሆነ ለግሪኮችም፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። 25ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፤ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 26ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው መመዘኛ ብዙዎች ጥበበኞች አልነበሩም፥ ብዙዎች ኀያላን አልነበሩም፥ ብዙዎች ታላላቅ ሰዎች አልነበሩም። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ 28እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ እና የተናቀውን ነገር፥ ያልሆነውንም ነገር መረጠ፤ 29ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። 30ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፥ ጽድቃችንና ቅድስናችንም ቤዛችንም በተደረገልን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። 31#ኤር. 9፥24።ስለዚህ፥ እንደተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ “የሚመካ በጌታ ይመካ፤”
Currently Selected:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in