YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14

14
የትንቢትና የልሳን ስጦታዎች
1ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፥ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። 2በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለሚናገር የሚረዳው የለም። 3ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፥ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። 4በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። 5ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፥ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።
6እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ፥ በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኩአችሁ ምን እጠቅማችሃለሁ? 7እንደዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች እንኳ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው ዜማቸውን እንዴት ማወቅ ይቻላል? 8ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ የሚታወቅ ቃል ካልወጣ፥ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። 10በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለውም ቋንቋ የለም። 11እንግዲህ የሚነገረውን ቋንቋ ትርጉሙን ካላወቅሁ፥ ለተናጋሪው እንግዳ እሆንበታለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆንብኛል። 12እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት የምትሹ በመሆናችሁ፥ ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ።
13ስለዚህ በልሳን የሚናገር ሰው የሚናገረውን መተርጐም እንዲችል ይጸልይ። 14በልሳን በምጸልይበት ጊዜ መንፈሴ ይጸልያል፤ አእምሮዬ ግን ፍሬ አልባ ነው። 15ታዲያ፥ ምን ማድረግ አለብኝ? በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። 16እንዲህማ ካልሆነ፥ በመንፈስ በምትባርክበት ጊዜ፥ አንተ የምትለውን የማያውቅ እንግዳ ሰው ካልተረዳ፥ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ፥ “አሜን” ሊል ይችላል? 17አንተ በሚገባ ታመሰግን ይሆናል፤ ሌላው ሰው ግን አይታነጽበትም። 18ከሁላችሁ የበለጠ በልሳን ስለምናገር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 19ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌሎችን ለማስተማር፥ ዐሥር ሺህ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ፥ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር ይሻላል።
20ወንድሞች ሆይ፤ በአስተሳሰባችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፉ ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአስተሳሰባችሁ ግን ጐልማሶች ሁኑ። 21#ኢሳ. 28፥11፤12።“ቋንቋቸው እንግዳ በሆነ ሰዎች፥ በባዕዳንም አንደበት ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም፥ ይላል ጌታ” ተብሎ በኦሪትም ተጽፎአል። 22በዚህ ዓይነት፥ በልሳን መናገር ለማያምኑ የሚሆን ምልክት እንጂ ለሚያምኑት አይደለም፤ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 23እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአንድነት በተሰበሰቡበት፥ ሁሉም በልሳን በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዶች ወይም የማያምኑ ሰዎች ወደ ጉባኤው ቢገቡ፥ አብደዋል አይሉምን? 24ነገር ግን ሁሉም ትንቢት በመናገር ላይ እያሉ፥ እንግዳ ወይም የማያምን ሰው ቢገባ፥ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይመረመራል፤ 25በልቡም የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ እንዲሁም፥ “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት በግንባሩ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።
ሥርዓት ያለው አምልኮ
26ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። 27በልሳን የሚናገር ቢኖር፥ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ አንዱ ደግሞ ይተርጉም፤ 28የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን፥ በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። 29ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። 30ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። 31እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፥ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። 32የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ 33እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ፥ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው።
34ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ 35ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፥ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በቤተ ክርስቲያን መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። 36የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን?
37ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ሰው ነኝ የሚል ቢኖር፥ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ 38ይህን አላውቅም የሚል ቢኖር እርሱም አይታወቅ። 39ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ 40ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ይሁን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in