YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11

11
1 # 1ሳሙ. 12፥12፤ 31፥11፤ 2ሳሙ. 10፥2። አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ያቢሽ ገለዓድን ከበባት፤ የያቢሽም ሰዎች ሁሉ ናዖስን፥ “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። 2አሞናዊው ናዖስ ግን፥ “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። 3የያቢሽም ሽማግሌዎች፥ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ ለአንተ እንገዛለን” አሉት። 4መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5በዚህ ጊዜ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከእርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፥ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የያቢሽ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። 6#1ሳሙ. 16፥13፤ መሳ. 14፥6፤ 19፤ 15፥14።ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ቁጣውም እጅግ ነደደ። 7#1ነገ. 11፥30፤ 2ነገ. 13፥18።ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቆራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፥ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቆራረጣል!” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከጌታ ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። 8ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሠራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቁጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺህ፥ ከይሁዳም ሠላሳ ሺህ ነበር። 9ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፥ “ለያቢሽ ገለዓድ ሰዎች፥ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለያቢሽ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ተደሰቱ። 10የያቢሽም ሰዎች፥ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው። 11በማግስቱ ሳኦል ሠራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳን ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ።
የሳኦል ንጉሥነት መረጋገጥ
12 # 1ሳሙ. 10፥27። ሕዝቡ ሳሙኤልን፥ “ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል! ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት። 13#2ሳሙ. 19፥23።ሳኦል ግን፥ “ይህ ዕለት ጌታ እስራኤልን የታደገበት ቀን ሰለሆነ፥ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ። 14ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፥ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውንም እናጽና” አለ። 15ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በጌታ ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት በጌታ ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ በታላቅ ደስታ አከበሩት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in