YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19

19
ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ማሳደዱ
1 # 1ሳሙ. 18፥1፤ 20፥1-3። ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። 2እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። 3እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” 4ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። 5#1ሳሙ. 17፥55-56፤ ዘዳ. 19፥10፤ መዝ. 119፥109።ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” 6ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። 7ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። 8እንደገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። 9#1ሳሙ. 16፥14፤ 18፥10-11።ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፥ ከጌታ ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ያንጊዜ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር። 10ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር እግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። 11#መዝ. 59።ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፥ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፥ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። 12#ኢያ. 2፥15፤ የሐዋ. 9፥25፤ 2ቆሮ. 11፥33።ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፥ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። 13#ዘፍ. 31፥19፤ መሳ. 17፥5፤ 18፥14፤ 18፤ 20፤ ሕዝ. 21፥26።ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። 14ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፥ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። 15ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፥ “እገድለው ዘንድ ከነአልጋው አምጡልኝ” አላቸው። 16የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ፥ እነሆ፥ የጣዖት ምስሉ በአልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጉር ተደርጎለት ነበር። 17ሳኦልም ሜልኮልን፥ “እንዲህ አድርገሽ ለምን አታለልሽኝ? ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፥ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ ያለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት። 18ዳዊት ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ፥ ወደ ራማ ወደ ሳሙኤል ሄደ፥ ሳኦል ያደረገበትን ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ወደ ናዮት ሄደው በዚያ ተቀመጡ። 19ለሳኦልም፥ “እነሆ፤ ዳዊት ራማ በምትገኘው በናዮት ተቀምጧል” ብለው ነገሩት። 20#1ሳሙ. 10፥5-6፤ 10፤ ዘኍ. 11፥25።ስለዚህ ዳዊትን እንዲይዙ ሰዎችን ላከ፤ እነርሱም የነቢያትም ጉባኤ በሳሙኤል መሪነት ትንቢት ሲናገሩ ባዩ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ሰዎች ላይ ወረደ፤ እነርሱም እንደዚሁ ትንቢት ተናገሩ። 21ሳኦልም ይህ በተነገረው ጊዜ ሌሎች ሰዎች ላከ፤ እነርሱም ትንቢት ተናገሩ፤ ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ ሰዎች ላከ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። 22በመጨረሻም፥ እርሱ ራሱ ወደ ራማ ሄደ፤ ከዚያም በሴኩ ወዳለው ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንደ ደረሰ፥ “ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። አንድ ሰውም “በራማ በምትገኘው የራማዋ ናዮት ናቸው” ብሎ ነገረው። 23ስለዚህ ሳኦል በራማ ወደምትገኘው ወደ የራማዋ ናዮት ሄደ፤ ሲሄድ ሳለም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ ደግሞ ወረደ፤ ወደ ናዮት እስኪደርስ ድረስም ትንቢት እየተናገረ ተጓዘ። 24#1ሳሙ. 10፥10-12፤ 2ሳሙ. 6፥20።እርሱም ልብሱን አውልቆ፥ በሳሙኤልም ፊት ደግሞ ትንቢት ተናገረ፤ በዚህ ሁኔታም ቀኑንና ሌሊቱን በሙሉ ራቁቱን ተጋደመ። ሕዝቡ፥ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት እንደ አንዱ ሆኖ ተቆጠረ?” ካለው የተነሣ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in