YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1

1
ሰላምታ
1በአዳኛችን በእግዚአብሔር በተስፋችንም በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ 2#የሐዋ. 16፥1።በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።
ከሐሰተኞች ትምህርት መጠበቅ
3ወደ መቄዶንያ በምሄድ ጊዜ በኤፌሶን ተቀምጠህ አንዳንድ ሰዎች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩ፥ 4ራሳቸውንም በተረት፥ መጨረሻም በሌለው የትውልዶች ታሪክ እንዳይጠመዱ እንድታዝ ለመንሁህ፤ ሆኖም ግን እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ከንቱ ምርምር ያመጣሉ እንጂ በእምነት የሚገኝውን የእግዚአብሔርን መጋቢነት አይጠቅሙም። 5የትእዛዙ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ኅሊና፤ ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር ነው፤ 6አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ፈቀቅ ብለው ወደ ከንቱ ንግግር በመሄድ፥ 7ምን እንደሚናገሩ ወይም በምን ዓይነት ነገሮች ላይ በድፍረት ማረገጋገጫ እንደሚሰጡ ሳያስተውሉ የሕግ አስተማሪዎች መሆንን ይፈልጋሉ።
8ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ ማንኛውም ሰው ለተጠቀመበት ሕግ መልካም እንደሆነ እናውቃለን፤ 9ይህንንም በመረዳት ሕግ የተሠራው ለጻድቃን ሳይሆን ይልቁንስ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዐመጸኞችና ለኀጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮች፥ 10ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለሐሰተኞችም፥ በውሸትም ለሚምሉና የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው። 11ይህም ትምህርት ለእኔ በአደራ ከተሰጠኝ ከብሩክ እግዚአብሔር ክቡር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።
ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ያቀረበው ምስጋና
12ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ብርታት የሰጠኝን ጌታችንን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤ 13#የሐዋ. 8፥3፤ 9፥4፤5።ይሁንና ከዚህ ቀደም ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም የነበርኩ ብሆንም እንኳ ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ፤ 14የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሆኑት ከእምነትና ከፍቅር ጋር እጅጉን በዛልኝ። 15“ኀጢአተኞችን ለማዳን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፤” የሚለው ቃል የታመነና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኀጢአተኞችም ዋነኛው እኔ ነኝ፤ 16ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ዋነኛ በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ በማሳየት፥ በእርሱ አምነው የዘለዓለም ሕይወትን ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን አደረገኝ፥ በእዚህም ምክንያት ምሕረትን አገኘሁ። 17ለዘመናትም ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ብቻውን አምላክ ለሆነው መፈራትና ክብር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን።
18ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ የተነገረውን ትንቢት ሁሉ መሠረት በማድረግ፥ በእነርሱ መልካም ውጊያን እንድትዋጋ ይህችን ትእዛዝ በአደራ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ 19ይህን በምታደርግበት ጊዜ ግን እምነትንና በጎ ኅሊናን ይዘህ ይሁን፤ አንዳንዶች ሕሊናን ወደ ጎን በማድረግ፥ በእምነት ረገድ በማዕበል እንደተሰባበረች መርከብ ጠፍተዋል፤ 20ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ከእነዚህ መካከል ናቸው፤ እነርሱም እንዳይሳደቡ ለማስተማር ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in