YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3

3
ኤጲስ ቆጶስ ለመሆን የሚያበቃ መመዘኛ
1“ማንም ኤጲስ ቆጶስነት ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል፤” የሚለው ቃል የታመነ ነው። 2#ቲቶ 1፥6-9።እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ ነቀፋ የሌለበት፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ በመጠን የሚኖር፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ በሥርዓት የሚሠራ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር ብቃት ያለው፥ 3የማይሰክር፥ የማይቆጣ ነገር ግን ታጋሽ የሆነ፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ገንዘብን የማያፈቅር፥ 4ልጆቹን በሚገባ አካሄድ ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 5ነገር ግን ማንም ሰው የራሱን ቤት ማስተዳደር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? 6በትዕቢት ተወጥሮ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። 7በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።
ዲያቆን ለመሆን የሚያበቃ መመዘኛ
8እንዲሁም ዲያቆናት መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፥ ቃላቸውን የማያጥፉ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ለገንዘብ የማይስገበገቡ፥ 9የእምነትን ምሥጢር በንጹሕ ኅሊና የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 10እነዚህም ደግሞ በመጀመሪያ ይፈተኑ፤ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 11እንዲሁም ሴቶች መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው፥ ሐሜተኞች ያልሆኑ፥ በመጠን የሚኖሩ፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 12ዲያቆናት ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመልካም እያስተዳደሩ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። 13በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው የተከበረ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ትልቅ መተማመንን ያገኛሉ።
የእምነታችን ታላቅ ምሥጢር
14ፈጥኜ ወደ አንተ ለመምጣት ተስፋ በማድረግ ይህን ጽፌልሃለሁ። 15ይህ ሳይሆን ቀርቶ ብዘገይ ግን፥ በዚህ በጻፍሁልህ ትእዛዝ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ የእውነት ዓምድና መሠረት በሆነችው በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ እንድታውቅ ነው። 16የሃይማኖታችን ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱም፦
በሥጋ ተገለጠ፥
በመንፈስ ጸደቀ፥
ለመላእክት ታየ፥
በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፥
በመላው ዓለም ታመነ፥
በክብር ዐረገ፥ የሚል ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in