YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12

12
ጳውሎስ ያየው ራእይ
1በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፥ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ። 2ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት፥ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ እስከ ሦስተኛ ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው አውቃለሁ። 3እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም እግዚአብሔር ይወቀው፥ 4ወደ ገነት ተነጠቀ፤ በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችለውን፥ ሰውም ሊናገር ያልተፈቀደለትን ነገር ሰማ። 5እንደዚህ ባለው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ደካማ ከመሆኔ ሌላ የምመካበት የለኝም። 6ልመካ ብፈልግ አልሞኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው፤ ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው ባለፈ የበለጥኩ አድርጎ እንዳያስበኝ ይህን ከመናገር እቆጠባለሁ። 7የዚህን ግልጠት ልዩ ጸባይ በማየት እንዳልታበይ፥ ሥጋዬን መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። 8ይህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 9እርሱ ግን፥ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ በድካም ፍጹም ይሆናል” አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል እንዲያድርብኝ በበለጠ ደስታ በድካሜ መመካትን እወዳለሁ። 10ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም፥ በመንገላታት፥ በችግር፥ በስደት፥ በጭንቀት፥ ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያንጊዜ እበረታለሁ።
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሰዎች ላይ የነበረው ወቀሳ
11በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ! ይህ እናንተ ግድ ስላላችሁኝ የሆነ ነው። እኔ ከምንም የማልቆጠር ብሆን እንኳን፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አላንስምና፥ በእርግጥም እናንተ ስለ እኔ መናገር ይገባችሁ ነበር። 12በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት፥ በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በተአምራትም፥ በትዕግሥት በመጽናትም በመካከላችሁ ተከናውኗል። 13እኔ ራሴ ሸክም ሆኜባችሁ ካልሆነ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን በምን አንሳችሁ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ።
14እነሆ፥ ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሸክም አልሆንባችሁም፤ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግም። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። 15እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን አወጣለሁ፤ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ፥ የናንተ ፍቅር እንዴት ያንሳል? 16ይሁን እንጂ እኔ አልከበድኳችሁም፤ ነገር ግን በብልጠት አታልዬ ያጠመድኳችሁ ሆኖ ተሰምቷችኋል። 17ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ እንኳ ለራሴ ተጠቅሜባችኋለሁን? 18ቲቶን ገፋፋሁት፤ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ ለራሱ ጥቅም አውሏችኋልን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? አንድ ዓይነት እርምጃስ አልወሰድንምን?
19ለእናንተ ስለ ራሳችን ሁልጊዜ መልስ የምንሰጥ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆቼ! እናንተን ለማነጽ ስንል ሁሉን እንናገራለን። 20ወደ እናንት ስመጣ፥ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባት ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኝነት፥ ሐሜት፥ ማሾክሾክ፥ ኩራት፥ ሁከትም ይኖር ይሆን ብዬ እሰጋለሁ። 21እንደገና ስመጣ በእናንተ ፊት አምላኬ ያዋርደኝ ይሆን እያልኩ፥ ከዚህ በፊት ስለ ሠሩት ኃጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኩሰት፥ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ ቀርተው እንዳላዝን እፈራለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in