ወደ ዕብራውያን 13
13
እግዚአብሔርን የሚያስደስት አገልግሎት
1እርስ በርሳችሁ መዋደዳችሁን ቀጥሉ። 2#ዘፍ. 18፥1-8፤ 19፥1-3፤ ጦቢ. 5፥4፤5።እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች በዚህ ሳቢያ ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል። 3እስረኞችን አብራችኋቸው እንደታሰረ ሆናችሁ አስቡ፤ እናንተም በሥጋ እንዳለ እያሰባችሁ የተጨነቁትንም እንደራሳችሁ አስቡ። 4#ጥበ. 3፥13።ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፥ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። 5#ዘዳ. 31፥6፤8፤ ኢያ. 1፥5።ሕይወታችሁ ከፍቅረ ንዋይ የጸዳ ይሁን፤ ነገር ግን እርሱ ራሱ “አልለቅህም፤ ከቶም አልተውህም፤” ብሎአልና ያላችሁ ይብቃችሁ። 6#መዝ. 27፥1-3፤ 118፥6።ስለዚህ በመተማመን፥
“ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?”
እንላለን።
7የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። 8ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፥ ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው። 9በልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ መልካም የሚሆነው ልባችሁ በጸጋ ቢጸና ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚኖሩትም እንኳን አልተጠቀሙም። 10መሠዊያ አለን፤ ሆኖም ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ ከእርሱ የመብላት መብት የላቸውም። 11#ዘሌ. 16፥27።ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት የእንስሶችን ደም ወደ ቅድስት ያቀርባል፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል። 12ስለዚህ ኢየሱስም በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። 13ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከ መውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ። 14በዚህ ነዋሪ የሆነች ከተማ የለችንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንፈልጋለን። 15እንግዲህ ዘወትር ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት አድርገን በእርሱ በኩል እናቅርብለት። 16እንዲሁም መልካም ማድረግንና ያላችሁን ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ። እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
17ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። እነርሱ እንደሚጠየቁበት አድርገው ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ፤ ይህንንም በደስታ እንጂ በኀዘን እንዳያደርጉት፥ አለበለዚያ አይጠቅማችሁም።
18ለእኛም ጸልዩልን። በነገር ሁሉ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ተረድተናል። 19ይልቁን ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን እንድታደርጉ አጥብቄ እለምናችኋለሁ።
ጸሎትና የመጨረሻ ሰላምታ
20በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፥ 21በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ትፈጽሙ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
22ወንድሞች ሆይ! ይህን በጥቂት ቃል የጻፍኩላችሁን የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ። 23ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ እወቁ፤ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ። 24ለመሪዎቻችሁ ሁሉ፥ ለቅዱሳንም ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ ያሉትም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 25ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን 13: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in