YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ወንጌል 15

15
የወይን ግንድና ቅርንጫፎቹ
1“እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2በእኔ ያለውን ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእንናተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ ማፍራት አትችሉም። 5እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። 6በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፤ ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፤ ያቃጥሉአቸውማል። 7በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ፤ ይሆንላችሁማል። 8ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ አባቴ ይከበራል። 9አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን፥ ደስታችሁም ፍጹም እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ።
12 # ዮሐ. 13፥34፤ 15፥17፤ 1ዮሐ. 3፥23፤ 2ዮሐ. 1፥5። “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ። 13ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። 14እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። 15ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። 16እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንደሚሰጣችሁ፥ እንድትሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬአችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። 17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዛችኋለሁ።
ዓለም ደቀ መዛሙርትን እንደሚጠላ
18“ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። 19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስላልሆናችሁ ዓለም ይጠላችኋል። 20#ማቴ. 10፥24፤ ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 13፥16።‘ባርያ ከጌታው አይበልጥም፤’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን ካሳደዱኝ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌንም ከጠበቁ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። 21ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ በስሜ ምክንያት ያደርጉባችኋል። 22እኔ መጥቼ ባልነገራቸው ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው ሰበብ የላቸውም። 23እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። 24ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተዋል፤ ጠልተውማል። 25#መዝ. 34፥19፤ 68፥5።ነገር ግን በሕጋቸው ‘በከንቱ ጠሉኝ’ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 26ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ፥ እርሱም ከአብ የሚወጣው የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ 27እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in