YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 18

18
1መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥
መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።
2ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፥
በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ።
3ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥
ነውርም ከስድብ ጋር።
4የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፥
የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው።
5የጻድቅ ፍርድ ይጠምም ዘንድ፥
ለኀጥእም ማድላት መልካም አይደለም።
6የሰነፍ ከንፈር በጥል ውስጥ ትገባለች፥
አፉም በትርን ትጠራለች።
7የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥
ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው።
8የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥
እርሱም እስከ ሆድ ጉርጆች ድረስ ይወርዳል።
9በሥራው ታካች የሚሆን
የሀብት አጥፊ ወንድም ነው።
10የጌታ ስም የጸና ግምብ ነው፥
ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።
11ለሀብታም ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፥
በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር።
12ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥
ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።
13 # ሲራ. 11፥8። ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ
ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል።
14የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፥
የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል?
15የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥
የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች።
16የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥
በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች።
17ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፥
ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል።
18ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥
በኃያላንም መካከል ትበይናለች።
19የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፥
ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው።
20የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል፥
ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል።
21ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፥
የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ።
22 # ሲራ. 26፥1-4። ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥
ከጌታም ሞገስን ይቀበላል።
23ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፥
ሀብታም ግን በድፍረት ይመልሳል።
24ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፥
ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in