YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮሜ ሰዎች 14

14
በወንድምህ ላይ አትፍረድ
1 # ቈላ. 2፥16። በእምነት የደከመውንም አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት። 2ሁሉን መብላት እንደሚችል የሚያምን አለ፤ በእምነት ደካማው ግን አትክልት ይበላል። 3የሚበላ የማይበላውን አይናቀው፤ የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። 4አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን ጌታ ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል።
5ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንደሚሻል ያስባል፤ ሌላው ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። 6አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው ለጌታ ብሎ ነው፤ የሚበላም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ እግዚአብሔርን ያመሰግናልና የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። 7ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፤ ለራሱም የሚሞት የለም፤ 8በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። 9ስለዚህ ነገር የሙታንንና የሕያዋን ጌታ እንዲሆን ክርስቶስ ሞቷልና፥ ሕያውም ሆኖአልና።
10 # 2ቆሮ. 5፥10። አንተም በወንድምህ ላይ ስለምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለምን ትንቃለህ? ሁላችን በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና።
11 # ኢሳ. 45፥23። “እኔ ሕያው ነኝ፤” ይላል ጌታ፤ “ጉልበት ሁሉ ለእኔ
ይንበረከካል፤ ልሳንም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፤”
ተብሎ ተጽፎአልና። 12እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።
ወንድምን ማሰናከል አይገባም
13እንግዲህ ከዚህ በኋላ አንዳችን በአንዳችን ላይ አንፍረድ፤ ነገር ግን ከመፍረድ ይልቅ ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይወስን። 14በራሱ ርኩስ የሆነ ነገር እንደሌለ በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ፤ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ምንም ርኩስ እንዲሆን ለሚቆጥር ለእርሱ ርኩስ ነው። 15ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው። 16እንግዲህ በእናንተ ያለው መልካም ነገር እንዲሰደብ አታድርጉ፤ 17የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። 18እንደዚህ አድርጎ ክርስቶስን የሚያገልግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛል፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። 19እንግዲህ የሰላም ነገርና እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን ነገር እንከተል። 20በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ነገር በራሱ ንጹሕ ነው፤ በመጠራጠር የተበላ እንደሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። 21ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወይም ማንኛውም ወንድምህ የሚሰናከልበትን ነገር አለማድረግ መልካም ነው። 22ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በቆጠረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ የተባረከ ነው። 23የሚጠራጠር ሰው ቢበላ ግን በእምነት ስላልሆነ ተኰንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in