YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮሜ ሰዎች 5

5
የጽድቅ ውጤቶች
1እንግዲህ በእምነት ስለጸደቅን፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን፤ 2በእርሱም በኩል ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባት ችለናል፤ በእግዚአብሔርም ክብር በተስፋ እንመካለን። 3በዚህ ብቻ ሳይሆን፥ መከራ ጽናትን እንደሚያስገኝ ስለምናውቅ በመከራም ጭምር እንመካለን፤ 4ጽናትም የተፈተነ ባሕርይን ያስገኝልናል፥ የተፈተነ ባሕርይም ተስፋን፤ 5ተስፋም ቅር አያሰኘንም፤ ምክንያቱም በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ነው።
6ገና ደካሞች ሳለን፥ በትክክለኛው ጊዜ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቷልና። 7ስለ ጻድቅ ሰው ሲል የሚሞት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ስለ መልካም ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። 8ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። 9እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን ይበልጡንም በእርሱ በኩል ከቁጣ እንድናለን። 10ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ 11ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን።
አዳምና ክርስቶስ
12 # ዘፍ. 3፥6፤ ጥበ. 2፥24። ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ፥ ሞትም በኃጢአት በኩል እንደመጣ፥ እንዲሁም ሁሉም ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ 13ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበረና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም። 14ነገር ግን ለሚመጣው ምሳሌ እንደነበረው እንደ አዳም ሕግን ባልተላለፉት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ።
15ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ከሞቱ፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ያለው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት ይበዛ። 16ስጦታውም አንድ ሰው ኃጢአትን በማድረጉ እንዳመጣው ውጤት አይደለም፤ በአንድ በኩል፥ ፍርዱ የአንድን ሰው በደል ተከትሎ ኩነኔን አመጣ፤ በሌላ በኩል ግን ስጦታው ብዙ በደልን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። 17በአንድ ሰው በደል ምክንያት በዚህ ሰው በኩል ሞት ከነገሠ፥ ይልቁን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅን ስጦታ የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።
18 # 1ቆሮ. 15፥21-22። እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኩነኔ ለሰው ሁሉ እንደመጣ፥ እንዲሁም በአንድ ሰው የጽድቅ ሥራ ምክንያት ሕይወትን ለማጽደቅ መጣ። 19በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። 20በደል እንዲበዛ ሕግ ገባ፤ ነገር ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ጸጋ ይበልጥ በዛ፤ 21ይህም የሆነው፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ሕይወት፥ በጽድቅ በኩል እንዲነግሥ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in