YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮሜ ሰዎች 7

7
የጋብቻ ንፅፅር
1ወንድሞች ሆይ! ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና፤ ሕግ ሰውን የሚገዛው በሕይወት እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን አታውቁምን? 2ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ በሕግ ታስራለችና፤ ባሏ ቢሞት ግን ከባል ሕግ ተፈትታለች። 3ስለዚህ ባሏ በሕይወት እያለ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ ትባላለች። ባሏ ቢሞት ግን ከሕጉ ነፃ ናት፥ ሌላ ባል ብታገባ አመንዝራ አይደለችም።
4ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ እንድትሆኑና ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ ነው። 5በሥጋ እያለን የኃጢአት ሥቃይ በሕግ በኩል ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በሰውነታችን ክፍሎች ይሠራ ነበር። 6አሁን ግን ለእርሱ ታስረን ከነበርንበት በመሞት ከሕግ ተፈትተናል#7፥6 ነፃ ወጥተናል፤ ስለዚህም በአሮጌው በፊደል ሳይሆን በአዲስ በመንፈስ ኑሮ እናገለግላለን።
ሕግና ኃጢአት
7 # ዘፀ. 20፥17፤ ዘዳ. 5፥21። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? በጭራሽ! ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ ኃጢአትን አላውቅም ነበር፤ ሕጉ “አትመኝ” ባይል ኖሮ ምኞትን አላውቅም ነበር። 8ኃጢአት ግን በትእዛዝ አማካኝነት አጋጣሚን በመውሰድ ሁሉንም ዓይነት ምኞትን አስነሣ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ የሞተ ነውና። 9እኔም ድሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ። 10እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠው ትእዛዝ ለሞት መሆኑን ተገነዘብሁ፤ 11#ዘፍ. 3፥13።ኃጢአት በትእዛዝ በኩል አጋጣሚ አግኝቶ አታልሎኛልና፥ በእርሱም ገደለኝ። 12ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፥ ትክክለኛና መልካም ነው።
13እንግዲህ መልካም የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? በጭራሽ! ነገር ግን ኃጢአት ኃጢአትነቱ እንዲታይ፥ መልካም በሆነው ነገር ሞትን ይሠራብኝ ነበር። ይኸውም ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት ያለ ልክ ኃጢአት እንዲሆን ነው።
በሰው ሕይወት ውስጥ ያለ ትግል
14ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። 15#ገላ. 5፥17።ምን እየሠራሁ እንደሆነ አላውቅም፤ የምፈልገውን ነገር አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ነገር አደርጋለሁና። 16እንግዲህ የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ ሕግ ትክክል ነው እላለሁ። 17እንግዲህ አሁን ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን፥ በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። 18በእኔ ማለትም በሥጋዬ ምንም መልካም ነገር እንደማይኖር አውቃለሁና፤ መልካምን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም ነገር ግን ልፈፅመው አልችልም። 19ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፥ ነገር ግን ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁና። 20የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ፥ ያን የማደርገው እኔ ሳልሆን በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው።
21ስለዚህ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፋት ወደ እኔ ይቀርባል፤ ይኸውም ሕግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። 22በውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ 23ነገር ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ክፍሎች ባለ በኃጢአት ሕግ ምርኮኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች አያለሁ። 24እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? 25በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባርያ ስሆን፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባርያ ነኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ወደ ሮሜ ሰዎች 7