YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ሩት 2

2
ሩት በቦዔዝ እርሻ ልትቃርም መሰማራትዋ
1ለናዖሚም በባልዋ የሚዛመዳት ሰው ከኤሊሜሌክ ወገን የሆነ ስሙ ቦዔዝ የተባለ ኃያል ሰው ነበረ።#ሩት 3፥2፤ ማቴ. 1፥5። 2ሞአባዊቱም ሩት ናዖሚንን፦ “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው ተከትዬ እህል ለመቃረም#2፥2 ሀ፦ በሕጉ መሠረት ድሆች የዚህ መብት ነበራቸው፥ ይሁን እንጂ በዚህ ለመጠቀም የባለንብርቱ በጎ ፈቃድ አስፈላጊ ነበር። ወደ እርሻ ልሂድ” አለቻት። እርሷም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሂጂ” አለቻት። 3ስለዚህም ሄደች፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፥ እንደ አጋጣሚም የኤሊሜሌክ ወገን ወደነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። 4ከጥቂት ጊዜ በኋላም፥ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ ይባርክህ” ብለው መለሱለት። 5ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን አገልጋዩን፦ “ይህች ብላቴና የማን ናት?” አለው።#2፥5 ለ፦ በጥንታዊው የምሥራቅ ባህል እያንዳንዱዋ ሴት የአንዱ ነበረች፤ የአባት፥ የባል፥ የወንድም ወይም የጌታ። 6የአጫጆቹም አዛዥ፦ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከናዖሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ብላቴና ናት፥” ብሎ መለሰ።#ሩት 1፥22። 7“እርሷም፦ ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ’ ብላ፥ መጣች፤ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም” አለው።
8ቦዔዝም ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን አገልጋዮቼን ተከትለሽ ቃርሚ። 9ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፥ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፥ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ” አላት። 10በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት፦ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለሁ፥ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ፥ እንዴት በፊትህ ሞገስ አገኘሁ?” አለችው። 11ቦዔዝም፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ።#ሩት 1፥14-17። 12ለሠራሽው ሥራ ጌታ ይክፈልሽ፥ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በጌታ ዘንድ ዋጋሽ ፍጹም ይሁን” አላት።#ሩት 3፥9፤ ዘዳ. 32፥37፤ መዝ. 91፥4። 13እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባርያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ” አለችው።
14በምሳ ሰዓትም ቦዔዝ፦ “ወደዚህ ቅረቢ፥ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሺ አላት።#2፥14 በዚህ ዓውድ ወይን ጠጅ፥ የሚኮመጥጥ ወይም የሚያሰክር መጠጥ ከውሃ ጋር ቀላቅሎ መጠጣት በናዝራውያን በኩል የተከለከለ ነበር፤ ዘኁ 6፥3።” በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ ተረፋትም። 15ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ብላቴኖቹን፦ “በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አትከልክሏት፥ 16ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፥ እርሷም ትቃርም፤ አትከልክሉአትም” ብሎ አዘዛቸው።
17በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፥ የቃረመችውንም ወቃችው፥ ዐሥር ኪሎ ያህልም ገብስ ሆነ። 18ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፥ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። 19አማትዋም፦ “ዛሬ ከየት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን” አለቻት። እርሷም፦ “ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል” ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማቷ ነገረቻት። 20ናዖሚም ምራትዋን፦ “በሕያዋን እና በሙታን ላይ ቸርነቱ የማያልቅበት ጌታ የተባረከ ይሁን” አለቻት። ናዖሚም ደግሞ፦ “ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን#2፥20 ሊዋጁን። ከሚችሉት አንዱ ነው” አለቻት።#ዘፍ. 24፥27፤ ዘሌ. 25፥25፤ 27፥9-33። 21ሞዓባዊቱ ሩትም፦ “ደግሞ፥ መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ፥ አለኝ” አለቻት። 22ናዖሚም ምራትዋን ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ከሴት አገልጋዮቹ ጋር ብትወጪ ይሻላል፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው” አለቻት። 23ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝ ሠራተኞች አጠገብ እየቃረመች ቈየች፥ ከአማቷም ሳትለይ አብራ ተቀመጠች።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in