ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 12
12
ከመንፈስ ቅዱስ ስለሚገኙ ሀብታት
1ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታም ታውቁ ዘንድ እንጂ አላዋቆች ልትሆኑ አንወድድም። 2ቀድሞም እናንተ አሕዛብ በነበራችሁ ጊዜ ዲዳዎች ጣዖታትን ታመልኩ እንደ ነበር፥ ጣዖትም በማምለክ ረክሳችሁ እንደ ነበር፥#“ጣዖትም በማምለክ ረክሳችሁ እንደ ነበረ” የሚለው በግሪኩ የለም። ወደ ወሰዱአችሁም ትሄዱ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። 3ስለዚህም ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር፥ “ኢየሱስ ውጉዝ ነው” የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል አንድስ እንኳን እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ።
4መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው። 5ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። 6ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ። 7ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፤ 8በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፤ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ። 9ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ 10ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። 11#ሮሜ 12፥6-8። በዚህም ሁሉ ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይረዳል፤ ለሁሉም እንደ ወደደ ያድላቸዋል።
12 #
ሮሜ 12፥4-5። አካል አንድ እንደ ሆነ ብዙ የአካል ክፍሎችም እንደ አሉበት፥ ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 13እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል፤ አይሁድ ብንሆን፥ አረማውያንም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና። 14የአካላችንም ክፍሉ ብዙ ነው እንጂ አንድ አይደለም። 15እግርም፥ “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? 16ጆሮም፥ “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? 17አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ መስማት ከየት በተገኘ ነበር፤ አካልስ ሁሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ ማሽተት ከየት በተገኘ ነበር? 18አሁን ግን እግዚአብሔር የአካላችንን ክፍል በሰውነታችን ውስጥ እርሱ እንደ ወደደ እየራሱ አከናውኖ መደበው። 19የአካል ክፍሉ አንድ ቢሆን ኖሮ አካል የት በተገኘ ነበር? 20አሁንም የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው ፤ አካሉ ግን አንድ ነው። 21ዐይን እጅን፥ “አልፈልግሽም” ልትላት አትችልም፤ ራስም፥ “እግሮችን አልፈልጋችሁም” ልትላቸው አትችልም። 22ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉህ ናቸው። 23ከአካልም ክፍሎች የተናቁ ለሚመስሉን ክብርን እንጨምርላቸዋለን፤ ለምናፍርባቸውም የአካል ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል። 24ለከበረው የአካላችን ክፍል ክብርን አንሻለትም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውነታችንን አስማምቶታል፤ ይልቁንም ታናሹን የአካል ክፍል አክብሮታል። 25የአካላችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዳይለያዩ፥ አካላችን ሳይነጣጠል በክብር እንዲተካከል አስማማው። 26አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም#በግሪኩ “ቢከብርም” ይላል። የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 27እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ። 28#ኤፌ. 4፥11። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሾማቸው አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም መምህራንን፥ ከዚህም በኋላ ተአምራትና ኀይል ማድረግ የተሰጣቸውን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ሀብት የተሰጣቸውን፥ የመርዳትም ሀብት የተሰጣቸውን፥ የመምራትና ቋንቋን የመናገር ሀብት የተሰጣቸውን ነው። 29በውኑ ሁሉ ሐዋርያትን ይሆናሉን? ሁሉስ ነቢያትን ይሆናሉን? ሁሉስ መምህራንን ይሆናሉን? ለሁሉስ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጣልን? 30ለሁሉስ የመፈወስ ሀብት ይሰጣልን? ሁሉስ በቋንቋ ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጕማሉን? 31ነገር ግን ለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ፤ ደግሞም የምትሻለውን መንገድ አስተምራችኋለሁ።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 12: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in