መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 5
5
የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤም መካከል ያደረገችው ተአምር
1ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱአት፤ ከአቤኔዜርም ወደ አዛጦን ይዘዋት መጡ። 2ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡአት፤ በዳጎንም አጠገብ አኖሩአት። 3በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፤ ወደ ዳጎንም ቤት ገቡ፤ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ወድቆ አገኙት፤ ዳጎንንም አንሥተው በስፍራው አቆሙት።#ግሪክ ሰባ. ሊ. የቍ. 6ን መጀመሪያ ክፍል ከዚህ ያስገባል። 4በነጋውም ማለዱ፤ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ፥ ሁለቱ እጆቹም ተቈርጠው እየራሳቸው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ ሁለቱ መሀል እጆቹም በወለሉ ላይ ወድቀው ነበር። የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር። 5ስለዚህም የዳጎን ካህናት፥ ወደ ዳጎን ቤት የሚገቡትም ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም፤ ይራመዱት ነበር እንጂ።
6የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፤ ክፉም ነገር አመጣችባቸው፤ በእነርሱም ላይ በመርከቦች ውስጥ ወጣ፤ የአዛጦንንና የአውራጃዎችዋንም ሰዎች የውስጥ አካላቸውን በዕባጭ መታ፤ በከተሞቻቸውም መካከል አይጦች ወጡ፤ በከተማውም ታላቅ መቅሠፍት ሆነ። 7የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ፥ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አትቀመጥ” አሉ። 8ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ወደ እነርሱ ሰበሰቡና፥ “በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ?” አሉ፤ የጌት ሰዎችም፥ “የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ እኛ ትዙር” ብለው መለሱ። የእስራኤል አምላክ ታቦትም ወደ ጌት ሄደች። 9ከሄደችም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ መጣች፤ ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ታላቁንም ታናሹንም መታ፤ የውስጥ አካላቸውንም በእባጭ መታቸው፤ የጌት ሰዎችም የውስጥ አካላቸውን ምስል ሠሩ፥#“የጌት ሰዎችም የውስጥ አካላቸውን ምስል ሠሩ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. ብቻ። 10የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ላኩአት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣች ጊዜ አስቀሎናውያን፥ “እኛንና ሕዝባችንን ልታስገድሉን የእስራኤልን አምላክ ታቦት ለምን አመጣችሁብን?” ብለው ጮኹ። 11ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱአት፤ እኛንና ሕዝባችንን እንዳትገድል በስፍራዋ ትቀመጥ” አሉ። 12የእግዚአብሔር ታቦት ወደዚያ በገባች ጊዜ በከተማው ሁሉ ታላቅ ሁከት ሆኖአልና። በሕይወትም ያሉ፥ ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማዪቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 5: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in