ወደ ጢሞቴዎስ 1 2
2
የጸሎት ሥርዐት
1-2እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 3-4ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 5አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ 6ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፤ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤ 7እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ለመሆን ተሾምሁ፤ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም።
8እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ። 9-10እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። 11ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ 12ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም። 13አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። 14የተታለለም አዳም አይደለም፤ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች፤ 15ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች።
Currently Selected:
ወደ ጢሞቴዎስ 1 2: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in