YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ጢሞ​ቴ​ዎስ 1 3

3
ኤጲስ ቆጶስ ለመሆን የሚያበቃ መመዘኛ
1“ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል፤” የሚለው ቃል የታመነ ነው። 2እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ 3የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 4ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 5ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? 6በትዕቢት ተነፍቶ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። 7በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።
ዲያቆን ለመሆን የሚያበቃ መመዘኛ
8እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ለነውረኛ ረብ የማይስገበገቡ፥ 9በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 10እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፤ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 11እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፥ የማያሙ፥ ልከኞች፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 12ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። 13በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ።
የእምነታችን ታላቅ ምሥጢር
14ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። 15ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 16እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤
በሥጋ የተገለጠ፥
በመንፈስ የጸደቀ፥
ለመላእክት የታየ፥
በአሕዛብ የተሰበከ፥
በዓለም የታመነ፥
በክብር ያረገ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in